በክልሉ ዜጎችን በዲጂታል ክህሎት በማብቃት የሥራ ዕድልና ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ የተጀመሩ ተግባራት ይጠናከራሉ - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ዜጎችን በዲጂታል ክህሎት በማብቃት የሥራ ዕድልና ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ የተጀመሩ ተግባራት ይጠናከራሉ
ሆሳዕና፤ ጳጉሜን 5/2018 (ኢዜአ)፦በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዜጎችን በዲጂታል ክህሎት በማብቃት የሥራ ዕድልና ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ የተጀመሩ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አንተነህ ፈቃዱ ገለጹ።
በክልሉ "የነገ ቀን" የዲጂታል ልህቀት ለኢትዮጵያ ማንሰራራት! በሚል መሪ ሀሳብ በክልል ደረጃ በሆሳዕና ከተማ ተከብሯል።
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር፣ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የትምህርት ቢሮ ሀላፊ አቶ አንተነህ ፈቃዱ በዚሁ ወቅት እንዳሉት በክልሉ የዜጎችን ዲጂታል ክህሎት በማሳደግ የተወዳዳሪነት አድማስን ለማስፋት የተጀመሩ ተግባራት ይጠናከራሉ።
በተለይ በኢትዮ ኮደርስ ስልጠና ከ310 ሺህ 800 በላይ ዜጎች የተሳተፉ ሲሆን ስልጠናቸውን ያጠናቀቁ ከ237 ሺህ በላይ ሰልጣኞችም እውቅናና ምስክር ወረቀት አግኝተዋል ብለዋል።
ስልጠናው በዲጂታል ቴክኖሎጂ ብቁ የሆኑና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ሥራ ፈጣሪ ዜጎችን ለማፍራት አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።
አቶ አንተነህ እንደገለጹት በክልሉ የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥን ለማዘመን 7 መሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫዎች ተገንብተው ለአገልግሎት በመብቃታቸው የተገልጋይን እንግልት ማስቀረት ተችሏል ብለዋል።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ልዩ አማካሪ ንጉሴ አስረስ (ዶ/ር) በበኩላቸው በክልሉ በቴክኖሎጂ የተደገፈ አሰራርን በመተግበር የአገልግሎት ጥራትና ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ ሲሰራ ቆይቷል ብለዋል።
ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ በቴክኖሎጂ የበቃ ትውልድን የመገንባት ስራ አይነተኛ ሚና አለው ነው ያሉት፡፡
የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት አብድልሙህሲን ሀሰን (ዶ/ር) በበኩላቸው እንዳሉት የበለፀገች ሀገርን ለተተኪው ትውልድ ለማስተላለፍ በዲጂታል ቴክኖሎጂ የሰለጠነ የሰው ሀይል ግንባታ ላይ አተኩሮ መስራት ያስፈልጋል።
ለክልሉ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ሽግግር ስኬታማነት ዩኒቨርሲቲው የሚጠበቅበትን ድጋፍ እያበረከተ መሆኑንም ተናግረዋል።
በኢትዮ ኮደርስ ስልጠና ባገኘው እውቀት በቴክኖሎጂ የታገዘ የፈጠራ ሥራዎችን በማከናወን ተጠቃሚ መሆን እንደጀመረ የተናገረው ደግሞ በመድረኩ የተገኘው ወጣት ሙአዝ በድሩ ነው።
የነገ ቀንን በማስመልከት በተዘጋጀ የውይይት መድረክ የክልሉ፤ የዞንና የተለያዩ መዋቅሮች ከፍተኛ አመራሮች፣ ተማሪዎችና ተጋባዥ እንግዶች ተሳትፈዋል።