የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመገንባት ዲጂታል አሰራርን ማስፋፋት ዘመኑ የሚጠይቀው ጉዳይ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመገንባት ዲጂታል አሰራርን ማስፋፋት ዘመኑ የሚጠይቀው ጉዳይ ነው
ሚዛን አማን፤ ጳጉሜን 5/2018 (ኢዜአ)፦ የበለጸገች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የቴክኖሎጂ ሽግግርንና ዲጂታል አሰራርን ማስፋት የጊዜው ወሳኝ እርምጃ መሆኑ ተመላከተ።
ጳጉሜን 5 "የነገ ቀን" በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል በክልል ደረጃ በሚዛን አማን ከተማ በፓናል ውይይት ተከብሯል።
በመድረኩ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አልማው ዘውዴ፤ ነገን ለሚዋጀው የዲጂታል ቴክኖሎጂ ሥርዓት ባለፉት ዓመታት በዘርፉ የተከናወኑ ተግባራት ጠንካራ መሠረት የጣሉ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የበለጸገች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ቴክኖሎጂን መሠረት ያደረጉ ተግባራትን ማስፋፋት የጊዜው ወሳኝ ፍላጎት መሆኑን ተረድቶ ሁሉም ዜጋ ለዚህ አስፈላጊውን ዝግጅት ሊያደርግ እንደሚገባም አሳስበዋል።
በክልሉም በሁሉም የልማት መስኮች አሠራሮችን በማዘመን ፈጣን ዕድገትና ለውጥ ለማስመዝገብ የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።
የክልሉ ቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ቢሮ ኃላፊ ረዳት ፕሮፌሰር ዘመድኩን ሰሎሞን በበኩላቸው፤ ባለፉት ዓመታት የተመዘገቡ ስኬቶች ሀገራዊውን የ"ዲጂታል 2030" ራዕይ እውን ለማድረግ የሚያስችሉ ጠንካራ መሠረቶችን የጣሉ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በክልሉ የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና ወስደው ወደ ቴክኖሎጂ ፈጠራ ሥራዎች የገቡ ወጣቶች እየተፈጠሩ መምጣታቸውን የጠቆሙት ኃላፊው፤ እስካሁንም ከ1 ነጥብ 1 ሚሊዮን በላይ የክልሉ ነዋሪዎች የዲጂታል መታወቂያ ባለቤት መሆናቸውን ገልጸዋል።
በክልሉ በተደራጁ የመሶብ የአንድ ማዕከላት በኩል ከ50 በላይ አገልግሎቶች በዲጂታል መንገድ እየተሰጡ እንደሚገኝ የጠቆሙት ኃላፊው፤ በዚህም ዜጎች በቤታቸው ሆነው ወይም ማዕከላት ድረስ በመሄድ ፈጣን አገልግሎት ማግኘት መጀመራቸውን አክለዋል።
የውይይት ተሳታፊ የቤንች ሸኮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሀብታሙ ካፍትን በበኩላቸው፤ በዞኑ ደረጃ የአገልግሎት አሰጣጥ ሂደቱን ሙሉ በሙሉ ወደ ዲጂታል ሥርዓት ለማሸጋገር ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
በሚዛን አማን ከተማ የጀመሩት ሁለት የዲጂታል ማዕከላት ውጤታማ አገልግሎት መስጠት መቻላቸውን የጠቆሙት አቶ ሀብታሙ፤ ይህንን አሰራር ወደ ሌሎች የዞኑ ከተሞች ሙሉ በሙሉ ለማስፋት አስፈላጊው ዝግጅት መጠናቀቁንም አስረድተዋል።
በሚዛን አማን ከተማ በተካሄደው የጳጉሜን 5 "የነገ ቀን" የፓናል ውይይት መድረክ ላይ የክልልና የዞን ከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ በርካታ የመንግሥት ሠራተኞች ተገኝተዋል።