ቀጥታ፡

የነገውን ትውልድ ታሳቢ ያደረጉ ሰው ተኮር ፕሮጀክቶች ተጨባጭ ውጤት እየተገኘባቸው ነው

ደሴ ፤ ጳጉሜን 5/2018 (ኢዜአ)፦በደሴ ከተማ አስተዳደር እየተገነቡ የሚገኙና የነገውን ትውልድ ታሳቢ ያደረጉ ሰው ተኮር ፕሮጀክቶች ተጨባጭ ውጤት እየተመዘገበባቸው መሆኑን  የከተማው ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ሳሙኤል ሞላልኝ ገለጹ።

በደሴ ከተማ ጳጉሜን 5 ቀን "የነገ ቀን" በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል።

ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ሳሙኤል ሞላልኝ በዝግጅቱ ላይ እንደገለጹት፤ ከተማዋን በዲጂታል ቴክኖሎጂ በማበልጸግና አሰራርን በማዘመን ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል።


 

ከወረቀት ንክኪ ነፃ በሆኑ የቴክኖሎጂ አሰራሮች የመንግስት አገልግሎትን ለማሻሻል በተደረገው ጥረት "መሶብ የአንድ ማዕከል" አገልግሎት ተጨማሪ አቅም መፍጠሩንም ተናግረዋል።

የከተማዋን እድገት ለማፋጠን በተሰራው ስራም በኮሪደር ልማትና በሌሎች የነገውን ትውልድ ታሳቢ ባደረጉ ፕሮጀክቶች ተጨባጭ ውጤት ማስመዝገብ መቻሉን ገልጸዋል።


 

እንዲሁም የፈጠራ ሥራዎችን በማበረታታትና በመደገፍ ሀገራዊ እድገትን ለማፋጠን በከተማ አስተዳደሩ የተጀመረው ዲጂታል አሰራር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው ያብራሩት።

የከተማዋ ስማርት ሲቲ ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅና የደሴ መሶብ የአንድ ማዕከል አስተባባሪ አቶ ናትናኤል ከፍያለው በበኩላቸው፤ መሶብ የአንድ ማዕከል ከብልሹ አሰራር የጸዳና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት ማስቻሉን ገልጸዋል።


 

የስማርት ሲቲ ትግበራው የከተማዋን ሰላምና ደህንነት ማስጠበቅ የሚያስችል መሆኑን ጠቁመው፤ ማዕከሉ በአገልግሎት አሰጣጥ ዘርፍ የህብረተሰቡን እርካታ ማሳደጉን ተናግረዋል።

የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ሥራ መጀመሩ ህብረተሰቡ ፈጣንና ፍትሃዊ አገልግሎት እንዲያገኝ ማስቻሉንም አስረድተዋል።

ጳጉሜን 5 ቀን የነገን ቀን ምክንያት በማድረግ የደሴ ስማርት ሲቲ፣ የደሴ መሶብ የአንድ ማዕከልና ሌሎችም የቴክኖሎጂ ፕሮጀክቶች ጉብኝት ተካሂዷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም