ቀጥታ፡

በግንባታ ላይ ያሉ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች ለነገዋ ኢትዮጵያ ጠንካራ መሰረት የሚያኖሩ ናቸው- ወጣቶች

‎ጳጉሜን 5/2018 (ኢዜአ)፦ በግንባታ ላይ ያሉ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች ለነገዋ ኢትዮጵያ ጠንካራ መሰረት የሚያኖሩ መሆኑን በሀዋሳ ከተማ ኢዜአ ያነጋገራቸው ወጣቶች ገለጹ። 

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መጠናቀቁን ተከትሎ ሌሎች የሀገርን እድገትና ብልጽግና ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች በመከናወን ላይ ይገኛሉ።

በግንባታ ላይ ያሉ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ኢትዮጵያን በላቀ መልኩ ወደ ፊት የሚያራምዱ እና ለቀጣዩ ትውልድ ብሩህ ተስፋ የሰነቁ መሆናቸው ይታመናል። 

የነገዋን ኢትዮጵያ የሚወስኑት እነዚህ የልማት ፕሮጀክቶች ከሀገራዊ ፋይዳም የተሻገረ ቀጣናዊና አህጉራዊ ጠቀሜታ የሚኖራቸው ናቸው።

ከግዙፍ ፕሮጀክቶቹ መካከል የቢሾፍቱ አውሮፕላን ማረፊያ፣ የኒውኩለር ማብላያ፣ የጋዝ ፋብሪካ፣ ማዳበሪያ ፋብሪካ፣ የ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ይጠቀሳሉ።

እነዚህ ግዙፍ ፕሮጀክቶችና ሌሎችም እየተከናወኑ ያሉ ዘርፈ ብዙ የልማት ስራዎች የነገዋ ኢትዮጵያ ፅኑ መሰረትና የትውልዱ ብሩህ ተስፋ የሚሆኑ ናቸው።

በሌላ በኩል ወጣቱን ትውልድ በቴክኖሎጂ ተጠቃሚ በማድረግ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ እንዲሆን ለማስቻል እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች የነገዋን ኢትዮጵያ ለመገንባት መሰረት የሚጥሉ ናቸው።

በፖለቲካና ዲፕሎማሲ መስኮች የሚከናወኑ ሀገራዊ ጉዳዮችም የነገዋን የበለጸገች ኢትዮጰያ ለመገንባት ተስፋ የተሰነቀባቸው መሆኑን መግለፅ ይቻላል።

ከዚሁ ጋር በተገናኘ ኢዜአ ያነጋገራቸው የሀዋሳ ከተማ ወጣቶች በመደመር መንግስት እየተከናወኑ ያሉ ሀገራዊ ኢንሼቲቮችና ግዙፍ ፕሮጀክቶች የነገዋ ኢትዮጵያ ጠንካራ መሰረቶች መሆናቸውን ተናግረዋል።

ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል ወጣት በቃሉ መሠረት፤ ታላቁ የህዳሴ ግድብ፣ የጉባ ብስራቶች፣ የገበታ ፕሮጀክቶች፣ የኮሪደር ልማት ሥራዎችና ሌሎች ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ዛሬን ብቻ ሳይሆን ነገንም ጭምር ታሳቢ ያደረጉ መሆናቸውን አንስቷል።

የኢትዮጵያ የወደፊት እጣ ፈንታ ላይ ለመወሰን በተለይም የወጣቶች ጠንካራ ተሳትፎ አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሶ በዲጂታል ዘርፍ ግንባር ቀደም ተሳታፊ የሚሆንበት መደላድል መፈጠሩ ጥሩ ጅምር መሆኑን ተናግሯል።


 

ሌላኛው ወጣት ኃይለኢየሱስ ታምራት፤ በመደመር መንግስት እየተከናወኑ ካሉ ነገን ታሳቢ ያደረጉ ተግባራት መካከል የጠንካራ ተቋማት ግንባታ ሥራዎች ኢትዮጵያን ሊያሻግሩ የሚችሉ ናቸው ብሏል፡፡

ለአብነት በስኬት መከናወን የቻለው ሀገራዊ ምክክር በመነጋገር ላይ የተመሰረተ አዲስ የፖለቲካ ምዕራፍን የከፈተ ፣ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በዕኩልነት ለነገይቱ ኢትዮጵያ ሀሳብ ያዋጣበት መሆኑን ገልጿል፡፡

ወጣት ትዕግስት ፍስሀ በበኩሏ የመደመር መንግስት የኢትዮጵያ የህልውናና የነገ እጣ ፈንታ የሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮችንም በመተግበር በኢኮኖሚ የተሻለ ተወዳዳሪ የሆነች ሀገር ለመገንባት እየሰራ መሆኑን ተናግራለች፡፡   


                                                                                                                                                                                                                                                የባህር በር ባለቤትነትን ለማረጋገጥ አሁን ላይ እየተከናወኑ ያሉ ዓለም ዓቀፍ መርህን መሰረት ያደረጉ እንቅስቃሴዎች ኢትዮጵያን ከፍ የሚያደርጉ ተግባራት መሆናቸውን ጠቅሳለች፡፡

የባህር በር ባለቤትነት ለነገይቱ ኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ አንድምታ ያለው መሆኑን የተናገረችው ወጣት ትዕግስት፣ ለበርካታ ወጣቶች የሥራ ዕድል በመፍጠርና ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞች በማስገኘት ረገድ ትልቅ ተስፋ የሚጣልበት ተግባር መሆኑን አመላክታለች፡፡

መንግስት በሁሉም ዘርፎች እያከናወናቸው ያሉ ስኬታማ ተግባራት ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የበኩላቸውን እንደሚወጡ ወጣቶቹ አረጋግጠዋል፡፡

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም