ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ እየተመዘገበ ያለው ፈጣን እድገት በትውልዱ ዘንድ ብሩህ ተስፋ እና የላቀ ተነሳሽነት ፈጥሯል

ጂንካ፤ ጷግሜን 5/2018 (ኢዜአ፡-በኢትዮጵያ በየዘርፉ እየተመዘገበ ያለው ፈጣን እድገትና ለውጥ በትውልዱ ዘንድ ብሩህ ተስፋ እና የላቀ ተነሳሽነትን መፍጠሩን የጂንካ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።

በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የተገነቡና በግንባታ ላይ ያሉ ሜጋ ፕሮጀክቶቹ  የአሁኑን ትውልድ ብቻ ሳይሆን የመጪውን ብሩህ ጊዜ ታሳቢ ያደረጉ ስለመሆናቸውም ነዋሪዎቹ ተናግረዋል።

"የነገ ቀን"  ጳጉሜን-5  በሀገሪቱ በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ይገኛል፡፡

ቀኑን አስመልክቶ ኢዜአ በጂንካ ከተማ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች እንዳሉት ኢትዮጵያ በአጭር ጊዜ ውስጥ እያስመዘገበች ያለው  ፈጣን እድገትና ለውጥ ትውልዱ በነገዋ ኢትዮጵያ ቀን ብሩህ ተስፋ እንዲሰንቅ የላቀ ተነሳሽነት ፈጥሯል፡፡

ከነዋሪዎቹ መካከል የጂንካ ሁለተኛና መሰናዶ ትምህርት ቤት መምህር ሀብታሙ አያሌው እንዳሉት ሀገራችን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በግብርናው፣ በኢንዱስትሪ፣ በቴክኖሎጂና በቱሪዝም ዘርፎች ተጨባጭ የሆነ ፈጣን እድገት አስመዝግባለች።

በሀገሪቱ የተገነቡና እየተገነቡ ያሉ ሜጋ ፕሮጀክቶች ለነገዋ ኢትዮጵያና ለዜጎቿ ብሩህ ተስፋ መሆናቸውን ገልጸው፣ የሕዳሴው ግድብ፣ የቢሸፍቱ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት፣ የአረንጓዴ ልማት ሥራዎችና ሌሎች ግዙፍ ፕሮጀክቶች ሀገራዊ እድገትን በማፋጠን በየዘመኑ ትውልድን ተጠቃሚ ያደርጋሉ ብለዋል። 

በተለይ በአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር፣ በቱሪዝም ዘርፍ፣ በዲጂታል ኢትዮጵያ እና በገበታ ለሀገርና ለትውልድ የተከናወኑ ስኬታማ የልማት ተግባራት ተጨባጭ ለውጥ ያመጡና በትውልዱ ዘንድ ተነሳሽነትን የፈጠሩ ናቸው ብለዋል።


 

ሌላው የከተማው ነዋሪ አቶ ታምራት ምናስ፣ በኢትዮጵያ በመከናወን ላይ ያሉ ሜጋ ፕሮጀክቶች እና ዲጂታል ቴክኖሎጂ ለዜጎች ብዙ ተስፋና ዕድሎች ይዘው መጥተዋል ብለዋል።

በሴራ ያጣነውን የባህር በር ባለቤትነት የማስመለስ ጥረትን ጨምሮ ኢትዮጵያ ያላትን ሀብት በማልማት ከድህነት እንድትወጣ በተከናወኑ ሥራዎች እየተመዘገበ ያለው ውጤት በትውልዱ ዘንድ ተስፋን የሚያጭር ነው ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት በየዘርፉ እየተመዘገቡ ያሉ ስኬቶች መጪው ዘመን ለኢትዮጵያ ብሩህ እንደሆና ያሳያሉ ያሉት አቶ ታምራት፣ የኢትዮጵያን አድገት በላቀ ተነሳሽነት እና ትጋት ለማስቀጠል የበኩላቸውን ለመወጣት ዝግጁነታቸውን አረጋግጠዋል።


 

ወጣት በቃህኝ ጥላሁን በበኩሉ በኢትዮጵያ እየተከናወኑ ያሉ ትላልቅ ግዙፍ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች በወጣቱ ዘንድ ተስፋን ያጫሩ እና ለነገ ተነሳሽነቱን የያሳደጉ ናቸው ብሏል።

ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የተከናወኑ ሥራዎችና በመከናወን ላይ ያሉ ተግባራት ከሀጋራዊ ፋይዳቸው ባለፈ በተለይ ወጣቱን ከቴክኖሎጂ ጋር በማስተዋወቅ ተጠቃሚ እያደረጉ መሆናቸውን ተናግሯል። 

ወጣቱ በዲጂታል ኢትዮጵያ የቴክኖሎጂ አቅሙን ከማሳደግ ባለፈ ለሥራ ዕድል ፈጠራ በማዋል ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነቱን እያሳደገ ጭምር መምጣቱንም ገልጿል።

ኢትዮጵያ የተሻለች፣ የበለጸገች እና በቴክኖሎጂ ራሷን የቻለች ሀገር ለማድረግ ዛሬ እየተሰሩ ያሉ ሥራዎች የሀገሪቱን የነገ ብሩህ ተስፋ እያለመለሙ በመሆኑ መጠናከር እንዳለባቸው ተናግሯል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም