በክልሉ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂን ስኬታማ ለማድረግ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ይጠናከራሉ - ርዕሰ መስተዳድር ዓለሚቱ ኡሞድ - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂን ስኬታማ ለማድረግ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ይጠናከራሉ - ርዕሰ መስተዳድር ዓለሚቱ ኡሞድ
ጋምቤላ ፤ጳጉሜ 5/2018 (ኢዜአ)፡- በክልሉ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂን ስኬታማ ለማድረግ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ወይዘሮ ዓለሚቱ ኡሞድ ገለጹ።
ጳጉሜ 5 የነገ ቀን ’’የዲጂታል አብዮት ለነገዋ ኢትዮጵያ’’ በሚል መሪ ሃሳብ በጋምቤላ ከተማ በፓናል ውይይት ተከብሯል።
ርዕሰ መስተዳድሯ ዕለቱን አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂን ስኬታማ ለማድረግ የተጀመሩት ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።
በመደመር እሳቤ ባለፉት ዓመታት በቴክኖሎጂ ዘርፍ በተከናወኑ ተግባራት እንደ ክልልም ሆነ እንደ ሀገር በርካታ ውጤቶች መመዝገባቸውን አንስተዋል።
የዲጂታል ኢኮኖሚውን ስኬታማ ለማድረግ በኢትዮ-ኮደርስ ስልጠና እና በሌሎችም የክልሉን ወጣቶች በማሳተፍ የዲጂታል ቴክኖሎጂውን ዘርፍ ለማስፋት በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።
በተለይም የክልሉ ወጣቶች የቴክኖሎጂ ክህሎታቸውን በማዳበር በዲጂታል ኢኮኖሚው ግንባታ የበኩላቸውን ሚና ለመወጣት ጠንክረው ሊሰሩ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
በክልሉ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን፣ የሳይበር ደህንነትንና የዳታ አስተዳደርን በማጠናከር ለዜጎች ቀልጣፋና የዘመነ አገልግሎት ለመስጠት የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
የዕለቱ በዓልም በለውጡ ዓመታት የተመዘገቡትንና ለኢትዮጵያ ማንሰራራት መሰረት የጣሉ ስኬቶችን ለማብሰርና ለማጠናከር ያለመ መሆኑን ርዕሰ መስተዳድሯ ገልጸዋል።
የክልሉ ስራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊና የበዓሉ አስተባባሪ ኢንጂነር ጓነር ጆክ በዚሁ ጊዜ የነገ ቀንን ስናከብር በአዲስ ተስፋና ተነሳሽነት ሰው ተኮር አገልግሎቶችን ለማጠናከር መሆኑን ተናግረዋል።
በክብረ በዓሉ ላይ የክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችና የከተማው ነዋሪዎች የተገኙ ሲሆን በመርሃ ግብሩ ላይ ዕለቱን በማስመልከት የመነሻ ጽሁፍ ቀርቦ በተሳታፊዎች ውይይት ተደርጎበታል።