ቀጥታ፡

የሞጆ ሎጂስቲክስ ማዕከል የኢትዮጵያ የብልፅግና ጉዞ ማብሰሪያ፣ የቀጣናው ማስተሳሰሪያ እና የመደመር እሳቤ ፍሬ ማሳያ ነው

አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 5/2018 (ኢዜአ)፦ የሞጆ ሎጂስቲክስ ማዕከል የኢትዮጵያ የብልፅግና ጉዞ ማብሰሪያ፣ የቀጣናው ማስተሳሰሪያ እና የመደመር እሳቤ ፍሬ ማሳያ መሆኑን የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሞጆ የሎጂስቲክስ ማዕከል ማስፋፊያ መርቀው በይፋ ሥራ አስጀምረዋል።

በመርሀ ግብሩ ላይ ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር፣ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ፣ የኢፌዴሪ ጦር ሀይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ የሞጆ የሎጂስቲክስ ማዕከል የሀገራችን የደም ስር ነው።

የትራንስፖርትና የሎጂስቲክስ አገልግሎት ችግሮችን መፍታት የሚያስችል የማዕዘን ድንጋይ መሆኑን ገልጸዋል።

ማዕከሉ የሁለንተናዊ ልማትና ብልፅግና ማረጋገጫ የመደመር መንግሥት ስኬት አይነተኛ ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የዘርፉን ማነቆ በተመለከተ የሰጡት አቅጣጫ ፍሬ ማፍራቱ ማሳያ ነው ብለዋል።

የሞጆ ሎጂስቲክስ ማዕከል የኢትዮጵያ የብልፅግና ጉዞ ማብሰሪያ፣ የቀጣናው ማስተሳሰሪያ እና የመደመር እሳቤ ፍሬ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የአፍሪካ የሎጂስቲክ ማዕከል እናደርጋታለን ያሉት ቃል በተግባር እውን እንዲሆን ያስችላል ያሉት ሚኒስትሩ፤ በማዕከሉ ሁለት የባቡር መስመሮች መዘርጋታቸውን ተናግረዋል።

የወጭና ገቢ ንግድ ዕቃዎችን የሚያስተናግዱ መጋዘኖች የያዘና በአንድ ጊዜ በርካታ የጭነት አገልግሎት መስጠት ያስችላል ብለዋል።

አርሶ አደሮች ምርታቸው ሳይበላሽ ለውጭ ገበያ ማቅረብ የሚችሉበትን ዕድል መፍጠሩን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም