ቀጥታ፡

የሞጆ የሎጂስቲክስ ማዕከል በመደመር እይታ የሚመራው መንግሥት በሁሉም ዘርፎች ምርትና ምርታማነትን እያሳደገ ለመሆኑ ትልቅ ማሳያ ነው

አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 5/2018 (ኢዜአ)፦ የሞጆ የሎጂስቲክስ ማዕከል ማስፋፊያ ፕሮጀክት በመደመር እይታ የሚመራው መንግሥት በሁሉም ዘርፎች ምርትና ምርታማነትን እያሳደገ ለመሆኑ ትልቅ ማሳያ መሆኑን የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሞጆ የሎጂስቲክስ ማዕከል ማስፋፊያ ፕሮጀክትን መርቀው በይፋ ሥራ አስጀምረዋል።


 

በዚሁ የምርቃት መርሃ ግብር ላይ ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር፣ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ሽመልስ አብዲሳ፣ የኢፌዴሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው ከፍተኛ እንግዶች ተገኝተዋል።

የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ የመደመር መንግሥት ባለፉት ዓመታት በሁሉም ዘርፎች ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ፣ ጥራት ያለው ምርት ለማምረት እንዲሁም ምርቶችን ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያ በብቃት ለማቅረብ የመደመር እይታን መሠረት አድርጎ ሲሠራ ቆይቷል።

በግብርናና በኢንዱስትሪ ዘርፎች የሚመረቱ ምርቶች የሚፈለገውን የጥራት ደረጃ ጠብቀው ለገበያ እንዲቀርቡ በቂ የሎጂስቲክስ አቅርቦት አለመኖሩን አስታውሰዋል፡፡


 

ይህንን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ባለፉት ዓመታት በርካታ ሥራዎች መከናወናቸውን ጠቁመው፤ በተለይም ዘመናዊና በቂ የማከማቻ መጋዘኖች እንዲገነቡ፣ የመንገድ መሠረተ ልማቶች እንዲዘረጉ እና ለሎጂስቲክስ ዘርፉ አስፈላጊ የሆኑ ተሽከርካሪዎች እንዲቀርቡ መደረጉን ገልጸዋል።

ከዚህም በተጨማሪ እንደ አቮካዶና ሙዝ ያሉ በቀላሉ የሚበላሹ የግብርና ምርቶችን ጥራታቸውን ጠብቆ ወደ ውጭ ገበያ ለመላክ የሚያስችሉ የቀዝቃዛ ኮንቴይነሮችን ለማቅረብ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

ዛሬ በሞጆ ተመርቆ ሥራ የጀመረው ፕሮጀክት በምርታማነት ዘርፍ አዲስ ምዕራፍ የሚከፍትና የኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ከፍ የሚያደርግ ትልቅ ትርጉም ያለው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም