ቀጥታ፡

ሀገራዊ የምክክር ጉባዔ በስኬት መጠናቀቁ ለኢትዮጵያ አዲስ ምዕራፍ ከፋችና የተስፋ ብርሃን ያበሰረ ነው

አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 5/2018 (ኢዜአ)፦በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ አካታችና አሳታፊ የሆነው ሀገራዊ የምክክር ጉባዔ በስኬት መጠናቀቁ ለኢትዮጵያ አዲስ ምዕራፍ ከፋችና የተስፋ ብርሃን ያበሰረ መሆኑን የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ገለጹ።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በቀሪው የሥራ ጊዜው መጠናቀቅ ያለባቸውን ቀሪ ተግባራት እንደሚያከናውን አስታውቋል።


 

የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ በ2018 በዓመቱ የተከናወኑ ዓበይት ተግባራትን እና በቀሪው የሥራ ጊዜ የሚከናወኑ ዋና ዋና ተግባራትን አስመልክተው ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸው 2018 ዓ.ም በጀት ዓመት ስኬታማ ሆኖ ማለፉን ተናግረው፤ ከስኬቶች መካከል ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ በስኬት መጠናቀቁ ተጠቃሽ መሆኑን ተናግረዋል።

ከሐምሌ 8 እስከ ነሐሴ 16 ቀን 2018 ዓ.ም በተካሄደውና አራት ሺህ ተመካካሪዎች በተሳተፉበት ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ላይ በስምንት መሠረታዊ አጀንዳዎች ላይ ሰፊና ጥልቅ ምክክር መደረጉን አስታውሰው፤ በበርካታ ጉዳዮች ላይ ስምምነትና መግባባት ላይ መደረሱን ገልጸዋል።

ስለሆነም የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር በአሳታፊነት እና በአካታችነት በበርካታ ሀገራዊ እና መሠረታዊ በሆኑ አጀንዳዎች ላይ መክረው በመግባባት መከናወኑ የ2019 አብሳሪ እና አዲስ ምዕራፍ ከፋች ነው ብለዋል።


 

ይህ ስኬት ታሪክ ቀያሪ እና ተስፋ ሰጪ ውጤት ሙሉ የሚሆነው በአዲሱ የ2019 ዓ.ም እና ቀጥለው በሚኖሩ በርካታ አዳዲስ ዘመኖች ውጤታማነቱን አጠናክረን ስንቀጥል ብቻ ነው ብለዋል።

በመሆኑም ኮሚሽኑ በቀሪው የሥራ ጊዜው የምክክሩን ውጤት ከግብ ለማድረስ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሰራ ተናግረዋል።

በዚሁ መሠረት በኮሚሽኑ ማቋቋሚያ አዋጅ መሰረት ሌሎች መጠናቀቅ ያለባቸውን ቀሪ ተግባራት ያከናውናል ብለዋል።

እነሱንም አንደኛ የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ሂደቶችን፣ በምክክሮቹ የተገኙ ምክረ ሐሳቦችን ተግባር ላይ ሊውሉ የሚችሉበትን መንገድ የሚገልጽ ሰነድ በማዘጋጀት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ለአስፈጻሚ አካል እና ሌሎች ለሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት በቅርቡ እንደሚያቀርብ ገልጸው፤ ይህንም ለሕዝብ ይፋ ያደርጋል ሲሉ ጠቅሰዋል።

በሁለተኛ ደረጃ በሀገራዊ ምክክሮች የተገኙ ምክረ ሐሳቦችን መንግሥት በተግባር ላይ ለማዋል እንዲችል ግልጽ እና ተጨባጭ ኮሚሽኑን ማገዝ የሚያስችለውን ስትራቴጂ በመንደፍ ላይ ይገኛል ብለዋል።

በሦስተኛነት የምክረ ሐሳቦቹን አፈጻጸም ለመከታተል የሚያስችል ሥርዓት እና ዘዴዎችን ማዘጋጀት እና ማደራጀት እንደሆነም አመላክተዋል።

በአራተኛነት በክልሎች፣ በከተማ አስተዳደሮች እና በፌደራል ደረጃ ሊታዩ የሚገባቸውን ልዩነቶች ከኢትዮጵያ ሕዝብ እና ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጋር ማጠናቀቅ እንደሆነ ጠቅሰዋል።

አምስተኛው ሂደቶችን ግልጽ ለማድረግ፣ ግንዛቤ ለመፍጠር እና የምክክር ባህል ሆኖ እንዲቀጥል የሚያስችሉ የሕዝብ ግንኙነት እና የመገናኛ ብዙሃን ሥራዎችን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

እነዚሁ ቀሪ ተግባራት እንዲሳኩ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ በየደረጃው ያሉ የመንግሥት አካላት፣ የሃይማኖት፣ የሲቪክ፣ የከፍተኛ ትምህርት እና የመገናኛ ብዙሃን ሌሎች ተቋማት እና ማህበራት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ምሁራን እና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት የእስካሁኑን ስኬታማ አስተዋጽኦቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም