ዲጂታል የመንግስት አገልግሎትን በማስፋፋት የኢትዮጵያን ነገ ብሩህ ለማድረግ መሰረት ተጥሏል- ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ - ኢዜአ አማርኛ
ዲጂታል የመንግስት አገልግሎትን በማስፋፋት የኢትዮጵያን ነገ ብሩህ ለማድረግ መሰረት ተጥሏል- ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ
አርባ ምንጭ፣ ጳጉሜን 5/2018 (ኢዜአ)፡-ዲጂታል የመንግስት አገልግሎትን በማስፋፋት የኢትዮጵያን ነገ ብሩህ ለማድረግ መሰረት መጣሉን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ተናገሩ፡፡
ጳጉሜን-5 "የነገ ቀን" ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደን ጨምሮ የክልሉ፣ የዞንና የከተማ አስተዳደር የሥራ ሃላፊዎች እና ባለሙያዎች በተገኙበት በክልል ደረጃ በአርባ ምንጭ ከተማ እየተከበረ ይገኛል።
በመድረኩ ላይ ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ እንዳሉት በክልሉ ለህብረተሰቡ ቀልጣፋ የመንግስት አገልግሎት ለመስጠት ለዲጂታል አገልግሎት መስፋፋት ትኩረት ተሰጥቷል።
ዲጂታል 2030 ስትራቴጂን ለማሳካት በሰው ሀይል ልማትና በተቋማት ግንባታ ላይ ይበልጥ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
በተለይ ዲጂታል የመንግስት አገልግሎትን በማስፋፋት የኢትዮጵያን ነገ ብሩህ ለማድረግ መሰረት መጣሉን ገልጸዋል።
ለአብነትም መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ቀደም ሲል ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ የሚስተዋሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት ማስቻሉን ገልጸዋል።
ነገን የተሻለ ለማድረግ ኢትዮጵያ ዛሬ በየዘርፉ እያስመዘገበቻቸው ያሉ ስኬቶች የማንሰራራት ጉዞዋን እንደሚያቀላጥፈውም አመልክተዋል።
እንደ ሀገር የተጀመሩ ሜጋ ፕሮጀክቶችን እውን ለማድረግ የህብረተሰቡ ንቁ ተሳትፎ ቀጣይነት ባለው መልኩ መጠናከር እንዳለበትም አስገንዝበዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ቢሮ ሃላፊ ቦጋለ ቦሼ (ዶ/ር) በበኩላቸው እንዳሉት በክልሉ የዲጅታል አሠራር በመዘርጋቱ የዜጎችን ተጠቃሚነት ያረጋገጡ ለውጦች ተመዝግበዋል።
የተጀመረው የብልጽግና ጉዞ እንዲሳካ የዲጂታል ዘርፉ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል ያሉት ኃላፊው ዲጂታል 2030 ስትራቴጂን ለማሳካት በቅንጅት እንደሚሰራም አመልክተዋል።
በመድረኩ በዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስኬቶችና የወደፊት አቅጣጫዎች ላይ ያተኮረ ፓናል ውይይት ተካሂዷል፡፡