ሸገር ከተማ የህዝብ አገልግሎትን ለማዘመንና የነገ ከተማ ራዕይን ለማሳካት ዲጂታል ሽግግሯን እያፋጠነች ነው - ኢዜአ አማርኛ
ሸገር ከተማ የህዝብ አገልግሎትን ለማዘመንና የነገ ከተማ ራዕይን ለማሳካት ዲጂታል ሽግግሯን እያፋጠነች ነው
አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 5/2018 (ኢዜአ):-ሸገር ከተማ የህዝብ አገልግሎቷን ለማዘመንና የነገ ከተማ ራዕይን ለማሳካት ዲጂታል ሽግግሯን እያፋጠነች መሆኑን ከንቲባ ተሾመ አዱኛ (ዶ/ር) ገለጹ።
የሸገር ከተማ ከንቲባ ተሾመ አዱኛ (ዶ/ር) ጳጉሜን 5 የነገ ቀንን ምክንያት በማድረግ በኤካ ጣፎ ክፍለ ከተማ የተገነባውን የመሶብ የአንድ ማዕከል ዲጂታል አገልግሎት ህንፃን አስመርቀው ሥራ አስጀምረዋል፡፡
ከንቲባው በዚሁ ወቅት እንዳሉት ፤ ሸገር ከተማ የነገ ከተማ ራዕይን ለማሳካት ቴክኖሎጂን፣ ዲጂታላይዜሽንንና ዘላቂ የከተማ ልማትን በትኩረት እየተገበረች ነው።
ቴክኖሎጂ የሥራ ቅልጥፍናን ከማሳደግ ባለፈ ከህዝብ ጋር ያለውን ግንኙነትና የአገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል ወሳኝ ሚና እንዳለውም ተናግረዋል።
ከተማዋ ከተመሠረተች ጀምሮ የመሬት፣ የኢንቨስትመንትና የተለያዩ ዘርፎች መረጃዎችን ዲጂታል በማድረግ ላይ መሆኗን ከንቲባው ገልጸዋል።
በተጨማሪም የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት በከተማዋና በአራት ክፍለ ከተሞች እየተሰጠ ሲሆን፣ ከ280 ሺህ በላይ ዜጎች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
በኤካ ጣፎ ክፍለ ከተማ የተመረቀው የመሶብ ዲጂታል አገልግሎት ህንፃ የከተማዋን ዲጂታል ሽግግር በማጠናከር የህዝብ አገልግሎቷን ይበልጥ ለማዘመን ያግዛል።
ስለ ቴክኖሎጂ፣ ስለ ዲጂታላይዜሽንና ስለ ነገ ቀን ሳናስብ ምንም ዓይነት ውጤት መፍጠር አንችልም ሲሉም ከንቲባው አስገንዝበዋል።