ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በ60 ሄክታር መሬት ላይ የተገነባውን ዘመናዊ የሎጂስቲክስ ማዕከል ማስፋፊያ የመጀመሪያ ምዕራፍ መረቀው ከፈቱ - ኢዜአ አማርኛ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በ60 ሄክታር መሬት ላይ የተገነባውን ዘመናዊ የሎጂስቲክስ ማዕከል ማስፋፊያ የመጀመሪያ ምዕራፍ መረቀው ከፈቱ
አዲስ አበባ ፤ ጳጉሜን 5/2018 (ኢዜአ)፦ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በ60 ሄክታር መሬት ላይ የተገነባውን ዘመናዊ የሎጂስቲክስ ማዕከል ማስፋፊያ የመጀመሪያ ምዕራፍ መረቀው ከፍተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ በሞጆ ተገኝተው በምረቃው ላይ ባስተላለፉት መልዕክት ግንባታውን ኢትዮጵያ የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ጉዞ፡ በተግባር የታነጸበት ስራ ሲሉ ገልጸውታል።
ይህ ግዙፍ ፕሮጀክት በዓመት እስከ 1 ሚሊዮን ባለ 20 ጫማ ኮንቴነሮችን የማስተናገድ አቅም ያላቸው ጣቢያዎችና ዘመናዊ መጋዘኖች ያሉት መሆኑንም ገልጸዋል።
የደረቅ ብትን ጭነቶችን በሀገር ውስጥ እንድናሽግ ማስቻሉ፣ የውጭ ምንዛሬን ከመቆጠብ ባለፈ ለዜጎቻችን ሰፊ የሥራ ዕድል ይፈጥራል ብለዋል።
የማዕከሉን የአሰራር ፍጥነት ለማሳደግ በሀገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ የተተከለው የባቡር ላይ ክሬን ከባቡር መስመር የሚደረገውን የኮንቴነር ዝውውር በከፍተኛ ፍጥነት ያከናውናል ሲሉም ገልጸዋል።
ሙሉ አሰራሩ በዘመናዊ ዲጂታል መሰረተ ልማት የተሳሰረ በመሆኑ፣ ለተገልጋዮች ፈጣን እና አስተማማኝ አገልግሎትን ያሳልጣል።
ይህ ማዕከል ከኢትዮ-ጅቡቲ መስመር ባሻገር ኢትዮጵያን፣ ደቡብ ሱዳንን እና ዩጋንዳን የሚያስተሳስረው የ‘ደሱ’ ኮሪደር አካል ሲሆን፤ ይህም ሀገራችን በዓለም አቀፍ የሎጂስቲክስ ደረጃ ላይ ያላትን ስፍራ የሚያሻሽልና የቀጣናዊ የኢኮኖሚ ትስስራችንን ወደ አዲስ የዕድገት ምዕራፍ የሚያሸጋግር ትልቅ ድል ነው ብለዋል።