ቀጥታ፡

የአውሮፓ ህብረት ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን አጋርነት በአዲሱ ዓመት አጠናክሮ ይቀጥላል

ኢዲስ አበባ ፤ጳጉሜን 5/2018 (ኢዜአ)፦የአውሮፓ ህብረት ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን አጋርነት በአዲሱ ዓመት አጠናክሮ እንደሚቀጥል በኢትዮጵያ የአውሮፓ ህብረት አምባሳደር ሶፊ ፍሮም-ኤምስበርገር ገለፁ።

አምባሳደርዋ በኢትዮጵያ እና በአውሮፓ ህብረት መካከል እያደገ የመጣው አጋርነት ተስፋ ሰጪ መሆኑን በመግለጽ ለኢትዮጵያ ህዝብ የአዲስ ዓመት መልካም ምኞታቸውን አስተላልፈዋል።

አምባሳደር ሶፊ ፍሮም-ኤምስበርገር ለኢዜአ እንዳሉት፤ አገሪቷ ወደ 2019 ዓ.ም ስትሸጋገር ለኢትዮጵያውያን ሰላም፣ ብልፅግና፣ መልካም ጤንነትና ደስታን ተመኝተዋል።

የህብረቱ እና የኢትዮጵያ አጋርነት አሁን በመልካም መስመር ላይ እንደሚገኝ ገልፀው፤ የአውሮፓ ህብረት ለኢትዮጵያ አስተማማኝ እና ጠንካራ አጋር ነው ብለዋል።

በ2018 ዓ.ም በርካታ ከፍተኛ አመራሮች ያደረጓቸውን ጉብኝቶች እና የተጠናከሩ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ውይይቶችን ጨምሮ በህብረቱ እና በኢትዮጵያ ግንኙነት ውስጥ አስፈላጊ የሆኑ ዓበይት ኩነቶች የተመዘገቡበት እንደነበረ አንስተዋል።

አምባሳደሯ በ2018 ዓ.ም ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ በብራሰልስ ያደረጉትን ጉብኝት፣ እንዲሁም የአውሮፓ ህብረት የዓለም አቀፍ አጋርነት ኮሚሽነር ጁታ ኡርፒላይነን ለተሳካው የአውሮፓ ህብረት እና ኢትዮጵያ የንግድ ፎረም ወደ ኢትዮጵያ ያደረጉትን ጉብኝት ለአብነት ጠቅሰዋል።

በተጨማሪም በሐምሌ 2018 ዓ.ም የህብረቱ የውጭ ጉዳይ እና የደህንነት ፖሊሲ ከፍተኛ ተወካይ እንዲሁም የኮሚሽኑ ምክትል ፕሬዝዳንት ካጃ ካላስ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ከኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር እና ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጋር ያደረጉትን ውይይት አንስተዋል።

የተደረጉ ጉብኝቶችና ውይይቶች በፖለቲካዊ ልውውጦች ብቻ ሳይሆን በኢኮኖሚና ንግድ ጉዳዮች ያለውን ግንኙነት እየተጠናከረ መምጣቱን የሚያሳዩ ናቸው ሲሉ አምባሳደሯ ተናግረዋል።

በአውሮፓ ህብረትና በኢትዮጵያ መካከል ያለውን ፖለቲካዊ፣ ንግድና ኢንቨስትመንት፣ እንዲሁም ሁሉን አቀፍ ግንኙነት በአዲሱ 2019 የኢትዮጵያውያን ዓመትም የበለጠ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀዋል።

በዚህም  ከአውሮፓ በኩል የሚመጣውን ንግድና ኢንቨስትመንት በማሳደግ እንዲሁም ከሲቪል ማህበራት ጋር ያለንን ግንኙነት እናጠናክራለን ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም