የኢትዮጵያ ወደ ቀይ ባሕር መመለስ ለዓለም አቀፍ የባሕር ላይ ንግድ መስመር ደህንነት አስፈላጊ ነው - በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር አብርሃም ንጉሤ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ወደ ቀይ ባሕር መመለስ ለዓለም አቀፍ የባሕር ላይ ንግድ መስመር ደህንነት አስፈላጊ ነው - በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር አብርሃም ንጉሤ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 5/2018 (ኢዜአ):-የኢትዮጵያ ወደ ቀይ ባሕር መመለስ ለዓለም አቀፍ የባሕር ላይ ንግድ መስመር ደህንነት እና ለቀጣናው ኢኮኖሚ ዕድገት አስፈላጊ መሆኑን በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር አብርሃም ንጉሤ (ዶ/ር) ገለጹ።
እስራኤል የኢትዮጵያን የባሕር በር ባለቤትነት ሰላማዊና ዲፕሎማሲያዊ ጥያቄ የምትደግፈው መሆኑንም አስታውቀዋል።
አምባሳደር አብርሃም ንጉሴ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያ እና እስራኤል ታሪካዊ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ወደ ላቀ አጋርነት እየተሸጋገረ ነው።
በዚህም የመንግሥት ለመንግሥት፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እንዲሁም በንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፍ ከፍተኛ ዕድገት እየተመዘገበ መሆኑንም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በማደግ ላይ የምትገኝ ሀገር ናት ያሉት አምባሳደሩ፤ ለዚህም የኢትዮጵያን ወጪና ገቢ ንግድ የሚያሳልጥ የባሕር በር ከሌለ ዕድገትን ለማፋጠን አዳጋች ነው ብለዋል።
ለዚህም ኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነትን ለማረጋገጥ ላቀረበችው ሰላማዊና ዲፕሎማሲያዊ ጥረት እስራኤል በሙሉ ድጋፍ እንደምታደርግ አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ ወደ ቀይ ባሕር መመለስ የባሕር ላይ ሽብርተኞችንና ወንበዴዎችን በመመከት ለዓለም ሰላም እና የኢኮኖሚ ዕድገት ጥሩ ውጤት የሚያመጣ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት የሁለቱን ሀገራት ጂኦ ስትራቴጂክ ተጠቃሚነትን በማጎልበት ቀጣናዊ የሽብር ስጋቶችን በአስተማማኝ ሁኔታ ለመቀልበስ ጉልህ ፋይዳ እንደሚኖረውም አምባሳደሩ አስረድተዋል።
ሽብርተኞች በቀይ ባሕር ስትራቴጂክ የንግድ መስመር በመርከቦች ላይ በሚፈጽሙት ጥቃት ምክንያት በንግድ ስርዓቱ ላይ ሳንካ እየፈጠሩ መሆኑን ጠቁመዋል።
የእነዚህ የሽብር ኃይሎች እንቅስቃሴ ከኢትዮጵያ እና እስራኤል ባሻገር ለአውሮፓ፣ አሜሪካ፣ እስያና ለሌሎች ሀገራትም ጭምር የደህንነት ስጋት መሆኑን አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ መልስ ማግኘት መሰል የሽብር ኃይሎች እንቅስቃሴን በመግታት የኢኮኖሚና የደኅንነት ሉዓላዊነቷን ለማስጠበቅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለውም ነው አምባሳደር አብርሃም ንጉሴ (ዶ/ር) ያመላከቱት።
በመሆኑም የኢትዮጵያ አስተማማኝ ወደብ የማግኘት ሰላማዊና ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ተቀባይነት ያለውና እስራኤልም የምትደግፈው መሆኑን ጨምረው አረጋግጠዋል።
በተጨማሪም የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነትና ወደ ቀይ ባህር የመመለስ ምክንያታዊ ጥያቄ የምስራቅ አፍሪካ ቀጣናን ሰላምና ደኅንነት ለማስጠበቅ ብሎም ቀጣናውን በመሰረተ ልማትና በኢኮኖሚ ለማስተሳሰር ጉልህ ጠቀሜታ እንዳለው አንስተዋል።
ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር በየዓመቱ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞችን በመትከል ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን መቀነስ የሚያስችል አቅም እየፈጠረች እንደምትገኝም ገልጸዋል።
እስራኤልም በአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፎች ያላትን ልምድና ተሞክሮ በማጋራት ድጋፏን እንደምታጠናክር አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ ብዝኅ የተፈጥሮ ሃብት፣ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገትና አምራች የሰው ሃይል ከእስራኤል ቴክኖሎጂና ፈጠራ ትብብር ጋር በማቆራኘት ፈጣን ዕድገት ማስመዝገብ እንደሚያስችላት አንስተዋል።
ኢትዮጵያ በዓድዋ ድል ለአፍሪካውያን የነፃነት ምልክት እንደሆነችው ሁሉ፤ ድህነትንና ኋላ ቀርነትን በመግታት እንዲሁም በዲጂታል ሥርዓትና ብዝኅ ልማትም ፋና ወጊ መሆኗን ተናግረዋል።