የአዲስ አበባ ፈጣን የከተማ ለውጥ የሚያስደንቅ ነው - የጀርመኑ ዲፕሎማት - ኢዜአ አማርኛ
የአዲስ አበባ ፈጣን የከተማ ለውጥ የሚያስደንቅ ነው - የጀርመኑ ዲፕሎማት
አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 5/2018 (ኢዜአ)፦ በአዲስ አበባ እየተከናወኑ ያሉ ሁሉን አቀፍ የከተማ ልማት ስራዎች መዲናዋን በከፍተኛ ፍጥነት እንድትለወጥ ማድረጋቸውን በኢትዮጵያ የጀርመን ተጠባባቂ አምባሳደር ፈርዲናንድ ቮን ዌይሄ ገለጹ።
ዘመናዊ ኮሪደሮች፣ መልሰው ያገገሙ የወንዞች ዳርቻዎች፣ የህዝብ መዝናኛ ስፍራዎች እና እየሰፉ ያሉ አረንጓዴ ቦታዎች ለከተማዋ አዲስ መልክ መስጠታቸውን አምባሳደሩ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ ገልጸዋል።
ባለፉት ሶስት ዓመታት በአዲስ አበባ በቆዩባቸው ጊዜያት በከተማዋ የታዩ ለውጦች፣ በተለይም የኮሪደር ልማት ስራዎችንና ለህዝብ መዝናኛ ክፍት ቦታዎችን የማስፋት አጠቃላይ እንቅስቃሴን በቅርብ መከታተላቸውን ተናግረዋል።
በቆይታቸው የታዩ ተጨባጭ ለውጦችን መመልከታቸውንም ገልጸዋል።
የለውጡ ፍጥነት፣ የስራ ቁርጠኝነት እና ጥንካሬ የሚያስደንቅ መሆኑንም ነው የተናገሩት።
በአዲስ አበባ የሚከናወኑ የተለያዩ የልማት ስራዎች እርስ በእርሳቸው የተሳሰሩ እና ሰፊ የከተማ ፕላን እቅድን መሰረት ያደረጉ መሆናቸውን ለመገንዘብ እንደሚቻልም አመልክተዋል።
ሁሉም የኮሪደር ስራዎች እና የልማት እንቅስቃሴዎች አንዱ ከሌላው ጋር ተጣጥመውና ተቀናጅተው የሚከናወኑ መሆናቸውም የሚደነቅ ነው ብለዋል።
በቀበና ወንዝ አካባቢ፣ ከጀርመን ኤምባሲ አቅራቢያ አንስቶ እስከ ፈረንሳይ ኤምባሲ ድረስ ያሉትን ቦታዎች በመጥቀስ፣ እነዚህ ስፍራዎች የከተማዋ ገጽታ መለወጥ መገለጫዎች መሆናቸውን ጠቁመዋል።
ለውጦቹ በግንባታና በመሰረተ ልማት ላይ ብቻ የተወሰኑ እንዳልሆኑም ነው ያነሱት።
አሁን ላይ በርካታ ነዋሪዎች ከሰዓት በኋላ ጊዜያቸውን ከቤት ውጭ በማሳለፍ፣ በወንዞች ዳርቻዎች የእግር ጉዞ በማድረግ እና ህጻናትም በአዲሶቹ የብስክሌት መንገዶች እየተጠቀሙ መሆኑ ትልቅ ለውጥ ነው ብለዋል።
አምባሳደሩ የአዲስ አበባን የአረንጓዴ ልማት ስራዎች ከኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የተሳሰሩ መሆናቸውን ነው ያነሱት።
መርሃ ግብሩ የዛፍ ተከላ፣ የደን ልማት እና የአካባቢ ጥበቃን ከሀገሪቱ የልማት አጀንዳዎች ጋር የተቀናጀ መሆኑንም አድንቀዋል።
በግላቸው በመቶዎች የሚቆጠሩ ዛፎችን መትከላቸውንም አስታውሰዋል።
የአካባቢ ጥበቃ ሥራዎች ስኬት የተመሠረተው ዛፍ በመትከል ሂደቱ ላይ ብቻ ሳይሆን፣ ዛፉ እስኪጸድቅና ሙሉ ዕድገት እስኪያሳይ ድረስ በሚደረግ ቀጣይነት ያለው እንክብካቤ ላይ መሆኑን ከራሳቸው ተግባራዊ ልምድ መረዳታቸውን ገልጸዋል።
ዛፍ መትከል ብቻ ሳይሆን ዛፉ እያደገ ሲሄድ አብሮ መንከባከብና መከታተልን ይጠይቃል ብለዋል።