ቀጥታ፡

በበዓል ገበያ የኢንዱስትሪና የግብርና ምርቶች በቂ አቅርቦት በመኖሩ የተረጋጋ ግብይት እያካሄድን ነው -ሸማቾች

ሀዋሳ፣ ጳጉሜን 5/2018 (ኢዜአ):- በሀዋሳ ከተማ ለዘመን መለወጫ የበዓል ገበያ የኢንዱስትሪና የግብርና ምርቶች በቂ አቅርቦት በመኖሩ የተረጋጋ ግብይት እያካሄዱ መሆናቸውንሸማቾች ገለጹ ።

የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር በበኩሉ የአዲስ አመት ዘመን መለወጫ በዓልን ታሳቢ ያደረገ  አማራጭ የግብይት ማዕከላትን በማመቻቸት በቂ የምርት አቅርቦት እንዲኖር  ማድረጉን  አመልክቷል፡፡


 

ኢዜአ በከተማዋ በተለያዩ አከባቢዎች ተዘዋውሮ እንተደመለከተው የግብርናም ሆነ የኢንዱስትሪ ምርቶች በስፋት የቀረቡ ሲሆን በተመቻቹ አማራጭ የገበያ ማዕከላት ነዋሪዎች የበዓል ግብይታቸውን  እያካሄዱ ናቸው።


 

አስተያየታቸውን ከሰጡት ሸማቾች  መካከል ወይዘሮ መቅደስ ካሳሁን አስተዳደሩ ባመቻቸው የአማራጭ ግብይት ማዕከላት በቂ የሆነ የፋብሪካና የኢንደስትሪ ምርት አቅርቦት መኖሩን ጠቅሰዋል። 


 

በገበያው ከመደበኛው የበዓል ቅናሽ ዋጋ  በመኖሩ ሸቀጦችን  በተረጋጋ ሁኔታ እየተገበያዩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በከተማዋ የግብርናም ሆነ የኢንዱስትሪ ምርቶች በጥሩ ሁኔታ በመቅረባቸው የዋጋ ሁኔታም የተረጋጋ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ ሌላው ሸማች አቶ ኢሳያስ ከበደ የተባሉ ናቸው ።


 

በመደበኛው ገበያና በአማራጭ የግብይት  ማዕከላት  በማህበራት በኩል  ምርቶቻቸውን ማቅረባቸው  ሁሉም እንደአቅሙ  መሸመት የሚያስችል መሆኑን  ጠቁመዋል።

አስተዳደሩ ባመቻቸው የመሸጫ ቦታ  ከመደበኛው ገበያ በቅናሽ  ለሸማቹ እየሸጡ መሆኑን የተናገረችው  ደግሞ  ወይዘሪት ብሩክ ቃሬሶ ነች።


 

የአዲስ ዘመን የበዓል ገበያ የተረጋጋ መሆኑን የተናገሩት የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ሃላፊ አቶ አጋና ነቶ ለዚህም የተደረጉ ቅድመ ዝግጅቶች የላቀ ሚና መጫወታቸውን ተናግረዋል።

የበዓል ገበያውን የተረጋጋ ለማድረግ በምርት አቅርቦትና የዋጋ ቁጥጥርና ክትትል የሚያደርግ ከሰባት ተቋማትና የተለያዩ አካላት ያሉበት ግብረ ሀይል ተቋቁሞ ሲሰራ መቆየቱን ገልጸዋል።


 

በተለይም የምርት እጥረት እንዳይከሰት ከመደበኛ ገበያዎች በተጨማሪ አማራጭ የግብይት ማዕከላትን በማደራጀት አምራቹና ሸማቹ በቀጥታ የሚገናኙበት ሁኔታ በማመቻቸት ማህበረሰቡ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኝ መደረጉን ተናግዋል። 

የክትትልና ቁጥጥር ስርዓቱም በቅንጅት እየተሰራ እና በአጠቃላይ የበዓል ገበያ የተረጋጋ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም