ቀጥታ፡

ሰላምና ልማቷ የተረጋገጠ ኢትዮጵያን ለትውልድ ለማሻገር የጋራ ትብብር ያስፈልጋል- የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች

አዳማ፤ ጳጉሜን 5/2018 (ኢዜአ)፡-የኢትዮጵያን ዘላቂ ሰላምና ልማት ዕውን በማድረግ ለነገው ትውልድ ለማስተላለፍ የሁሉም አካላት የተቀናጀ ጥረትና አገራዊ ትብብር ወሳኝ መሆኑን ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ገለጹ።

በሀገሪቱ  አሁን ላይ የተያዙ የልማትና የሰላም ጥረቶች ፍሬ እንዲያፈሩ የፖለቲካ ልዩነቶችን ወደ ጎን በማለት በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ አብሮ መስራት ወሳኝ መሆኑን በተደጋጋሚ የሚገለጽ ጉዳይ ነው።

ጳጉሜ 5 «የነገ ቀን»ን አስመልከተው ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት በአዳማ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች እንዳሉት የኢትዮጵያን ዘላቂ ሰላምና ልማት ዕውን በማድረግ ለነገው ትውልድ ለማስተላለፍ የሁሉም አካላት የተቀናጀ ጥረትና አገራዊ ትብብር ወሳኝ ነው።

ከአስተያየት ሰጪዎች መካከል የአብን ሥራ አስፈጻሚና የኦሮሚያ ክልል አስተባባሪ አቶ ሀብታሙ ተሰማ፤ የጳጉሜን ቀናት በልማትና በመልካም አስተዳደር ተግባራት እንዲታሰቡ መደረጉ ሕዝባዊ ተግባቦትን ከማጎልበቱም በላይ ለነገው ትውልድ የተሻለች ሀገር ለማስረከብ ጉልህ አስተዋጽኦ አለው።

ሀገር በትውልድ ቅብብሎሽ የምትቀጥል በመሆኗ፣ መጻኢ ዕድሏን ብሩህ ለማድረግ በተለይም የወጣቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ባለቤትነት ማረጋገጥ አስፈላጊ መሆኑን አቶ ሀብታሙ ገልጸዋል።

የመደመር መንግሥት ካከናወናቸው ተግባራት መካከል የታላቁ ሕዳሴ ግድብ፣ የአረንጓዴ አሻራ፣ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዕድገትና የኮሪደር ልማትን ጨምሮ በመሠረተ ልማት ዘርፍ የተመዘገቡ ስኬቶች ከዛሬ ባለፈ የነገውን ትውልድ ታሳቢ ያደረጉ መሆናቸውን አንስተዋል።

በተለይም የመረጃ ሀብትን ከመጠበቅ ጎን ለጎን ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂን በመጠቀም የመንግሥት አገልግሎትን ለማዘመን በተጀመረው ሥራ፣ እንደ መሶብ ያሉ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት እየተስፋፉ እንደሚገኙ አክለው ገልጸዋል።

የባህር በር አጀንዳ እና የኢትዮ ኮደርስ ሥልጠና ፕሮጀክትም ትውልዱ ከመጪው ዘመን ቴክኖሎጂ ጋር እንዲራመድ የሚያስችሉና የኢትዮጵያ መንግሥት ነገን አርቆ የሚያይበት ማሳያ መሆናቸውን አቶ ሀብታሙ አብራርተዋል።

ስለሆነም ዘላቂ ሰላምና ሁለንተናዊ ልማቷ የተረጋገጠባትን ኢትዮጵያ ለነገው ትውልድ ለማስረከብ ሁሉም ወገን የበኩሉን ኃላፊነት ሊወጣ እንደሚገባ አሳስበዋል።


 

የመላው  ኢትዮጵያ አንድነት ድርጀት (መኢአድ) የምስራቅ ሸዋ ዞን አስተባባሪ አቶ ተድላ በቀለ በበኩላቸው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የጳጉሜ ቀናት የሀገርን መልካም እሴቶች በሚገነቡ የተለያዩ ሁነቶች መከበራቸው በጎ ጎን እንዳለው ገልጸዋል።

በመደመር መንግሥት በተጨባጭ የሚታዩ ልማቶች የተመዘገቡ ቢሆንም፣ ዘላቂ ሰላም ከማስፈን፣የዜጎች ደህንነት ከመጠበቅ፣ ከህብረተሰቡ የመልማት ፍላጎትና ከመሰረተ ልማት እጥረቶች የተነሳ  ከመንግስትና ከህዝቡ ብዙ መስራት እንደሚጠበቅ አስታውቀዋል።

በተለይም ህዝብን ለምሬት የሚዳርጉ ብልሹ  አሰራሮችና ሙስናን ቅድሚያ ሰጥቶ መታገል እንደሚገባ ጠቁመው፤  ለዚህም በየደረጃው ያለው ባለድርሻ አካል የበኩሉን አስተዋጽኦ በማድረግ ነገን ብሩህ ሊያደርጉ  ይገባል  ብለዋል።

ገዥው መንግስትም ከመልካም ተሞክሮዎችና ካጋጠሙት ፈተናዎች ትልቅ ትምህርት በመውሰድ እና በሆደ ሰፊነት በመታገስ ለዜጎች የሚታይ ተስፋን በመሰነቅ የነገን  ሰላም ለማስፈን ሊረባረብ ይገባል ነው ያሉት።

ለ2019 አዲስ ሕይወት ራሳችንን ማዘጋጀትና ለነገ የተሻለ ማኅበራዊ መስተጋብር፣ እውነተኛ ወንድማማችነት እና ዘላቂ ሰላም ለመገንባት በቁርጠኝነት መነሳት ያስፈልጋልም ብለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም