ቀጥታ፡

ትናንትን በመማርና በማረም ዛሬን በላቀ ትጋት በመገንባት ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን የዕለት ተዕለት ባህላችን እየሆነ ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ ጳጉሜን 5/2018 (ኢዜአ) ትናንትን በመማርና በማረም ዛሬን በላቀ ትጋት በመገንባት ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን የዕለት ተዕለት ባህላችን እየሆነ ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጳጉሜን 5 የነገ ቀንን አስመልክቶ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው መልዕክት አስተላልፈዋል።

በዚህ መልዕክታቸውም ከወረቀት ወደ ዲጂታል፤ ከተጠቃሚነት ወደ ፈጣሪነት ሲሉ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትናንትን በመማርና በማረም ዛሬን በላቀ ትጋት በመገንባት ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን የዕለት ተዕለት ባህላችን እየሆነ ነው ብለዋል።

ንግድና አገልግሎትን ያቀላጥፋል፣ መረጃዎችን ተደራሽ ያደርጋል፣ ዘርፎችንም ያዘምናል! ሲሉም ገልጸዋል።

5 ሚሊዮን ኢትዮጵያ ኮደሮች ንቅናቄ ወጣቶችን የሰው ሰራሽ አስተውሎት ፈጣሪ በማድረግ ወደ 7 ሚሊዮን ግባችን እያመራ ሲሆን የዲጂታል አገልግሎት ተደራሽነትና ጥራትን አረጋግጧል ብለዋል።

በሀገር በቀል አቅም የበለጸገው የሳይበር ሉዓላዊነታችን ደግሞ የማንቆጣጠራቸው ቴክኖሎጂዎችን ጥገኝነት አላቆ በዲጂታል ኢኮኖሚ በራስ አቅሟ የምትቆም አዲሷ ኢትዮጵያ በታላቅ ምዕራፍ ላይ መሆኗን በኩራት ያበስራል ሲሉም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም