ቀጥታ፡

የግብርናና የምግብ ሥርዓትን ማጠናከር ለአፍሪካ ዘላቂ ልማት ወሳኝ ነው

አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 4/2018 (ኢዜአ)፦የግብርናና የምግብ ሥርዓትን ማጠናከር አፍሪካ የአየር ንብረት ጫናን በመቋቋም ዘላቂ ልማቷን እንድታሳድግ ወሳኝ መሆኑ ተገለጸ። 

በአዲስ አበባ ከተማ ከጳጉሜን 2 እስከ 4 ቀን ሲካሄድ የቆየው አህጉራዊ ጉባኤ ፍጻሜውን አግኝቷል።

በጉባኤው ወቅት በአፍሪካ የግብርናና የምግብ ሥርዓትን ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር በማጣጣም የሕዝቦችን የምግብ ዋስትና እና የኑሮ ጽናት ለማሻሻል የሚያስችሉ ዋና ዋና አቅጣጫዎች ላይ ሰፊ ውይይት ተደርጓል። 

በዚሁ መድረክ ከ30 በላይ የአፍሪካ ሀገራት የተወጣጡ ተሳታፊዎች የተገኙ ሲሆን የአህጉሪቱን የግብርናና የምግብ አጀንዳ በዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ውይይቶች የበለጠ ማስገንዘብና ውሳኔዎችንም ወደ ተግባር ማሸጋገር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ መክረዋል።

የአፍሪካ የምግብ ሉዓላዊነት ህብረት (Alliance for Food Sovereignty in Africa - AFSA) አስተባባሪ ዶክተር ሚሊዮን በላይ እንደገለጹት፤ አፍሪካ በግብርናና በምግብ ሥርዓት ያላትን የራሷን ልምድና መፍትሔ በማጠናከር በአህጉርና በዓለም አቀፍ መድረኮች የራሷን አጀንዳ በተግባር ማስፈጸም ይገባታል። 

አህጉሪቱ በዘርፉ ያላትን መልካም ተሞክሮ የበለጠ ማጉላት እንዳለባት ጠቁመው ለተቋቋሚ የምግብ ሥርዓት ግንባታ አግሮ-ኢኮሎጂን ማስፋፋት፣ የገበሬዎችን የዘር ሀብት መጠበቅና የገበሬዎችን ተሞክሮ ከሳይንስ ጋር በማጣመር የተሻለ የግብርና ልማት ማምጣት እንደሚገባ አስረድተዋል። 

በተጨማሪም የአፈርና የውሃ ሀብትን በአግባቡ መጠቀም፣ የአካባቢ የምግብ ገበያዎችን ማጠናከርና አፍሪካ የምግብ ፍላጎቷን በተቻለ መጠን በራሷ ምርትና ሀብት በመሸፈን የምግብ ሉዓላዊነቷን ማረጋገጥ እንደሚገባት ገልጸዋል።

የምግብ ሥርዓቱ ቀጥተኛ ተዋናዮች ሀሳባቸው በውሳኔዎች ውስጥ እንዲንጸባረቅ የሚያስችል ተጨባጭ ተሳትፎ ሊኖራቸው እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡ 

ኢትዮጵያ በዘር ሀብት ጥበቃ፣ በአግሮ-ኢኮሎጂና በምግብ ሉዓላዊነት ያላትን ልምድ በማጠናከር ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ተሞክሮ ማካፈል እንደምትችል ጠቁመዋል፡፡

የአርሶ አደሮችን የዘር ሀብት መጠበቅና አሀጉራዊ ተሞክሮዎችን ከሳይንሳዊ እውቀት ጋር በማጣመር የተሻለ የግብርና ልማት ለማስመዝገብ መስራት እንደሚገባ አስረድተዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም