ቀጥታ፡

በአዲሱ ዓመት የማዕድ ማጋራትና የመደጋገፍ ባህልን ይበልጥ ማጎልበት ወሳኝ ነው

አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 4/2018 (ኢዜአ)፦ በአዲሱ ዓመት የማዕድ ማጋራትና የመደጋገፍ ባህልን ይበልጥ ማጎልበት እንደሚገባ በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የሚኒስትሩ አማካሪ አቶ ጌታቸው በዳኔ ገለጹ። 

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የዘመን መለወጫ በዓልንና  የሕብር ቀን ምክንያት በማድረግ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ በሚገኘው የሴቶች ማረፍያና ልማት ማኅበር ለሚገኙ ሴቶች ማዕድ አጋርቷል።

በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የሚኒስትር አማካሪ ጌታቸው በዳኔ በዚሁ ወቅት በሕብር ቀን ሚኒስቴሩ ለስርዓተ ጾታ እኩልነት  እና ለማህበራዊ ደህንነት መረጋገጥ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።


 

ለሀገር እድገት፣ ሰላምና ማህበራዊ መረጋጋት ከሚሰጡ ቅድሚያዎች መካከል አንዱ የሴቶችን መብት ማስከበር እንደሆነ አመልክተዋል።

የሴቶችን መብት ለማስጠበቅ ከሚደረገው ጥረት ጎን ለጎን፣ በተለያዩ ምክንያቶች ለጥቃትና ለችግር የተጋለጡ ሴቶችን የማህበራዊና ስነ-ልቦናዊ ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡

በዘላቂነት መልሶ ለማቋቋም የሚያግዙ ተግባራትን ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እያከናወነ እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡

በዛሬው ዕለትም በተለያዩ ምክንያቶች ጥቃት ለደረሰባቸው ሴቶች ማረፊያና ልማት ማኅበር የአንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር በዓይነትና በገንዘብ ድጋፍ መደረጉን ጠቅሰዋል፡፡ 


 

የሕብር ቀን አብሮነትንና ማህበራዊ ትስስርን ይበልጥ የሚጠናከርበትና የመደጋገፍ እሴትን በተግባር የሚገለጥበት መሆኑን ተናግረዋል።

የዛሬው ማዕድ ማጋራትም እርስ በእርስ የመረዳዳት ባህል የሚያሳይ፣ አዲሱን ዓመት በተስፋ፣ በደስታ እና በሙሉ ስነ-ልቦናዊ ዝግጅት ለመቀበል እንዲያስችል መሆኑን ተናግረዋል።

ዛሬ የተደረገው የበጎ አድራጎት ተግባርም ይህንን ታሪካዊ እሴት በመጠበቅ ለሚመጣው ትውልድ ለማስተላለፍ ያለመ መሆኑን ገልጸዋል።

የሴቶች ማረፍያና ልማት ማኅበር ዋና ዳይሬክተርና መስራች ማርያ ሙኒር በበኩላቸው፤ በተደረገው ድጋፍ መደሰታቸውን ገልጸው፣ ለዚህም በተጠቃሚዎች ስም ምስጋና አቅርበዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም