ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ከዕዳ ተላቆ ወደ ውጤታማ የትርፋማነት ምዕራፍ ተሸጋግሯል - ኢንጂነር አሸብር ባልቻ

አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 4 /2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ከነበረበት ዕዳ ተላቆ ወደ የትርፋማነት ምዕራፍ መሸጋገሩን የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ አስታወቁ።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አመራርና ሠራተኞቹ በተገኙበት የዘንድሮውን የ2018 በጀት ዓመት "ንጹህ ኢነርጂ ለተሻለ ሕይወት" በሚል መሪ ሐሳብ የተቋም ቀኑን አክብሯል።


 

ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ በዚህ ወቅት፤ ኤሌክትሪክ ኃይል ኢትዮጵያን የአፍሪካ የታዳሽ ኃይል ማዕከል የማድረግ ራዕይ የሚያሳካ ውጤት እያስመዘገበ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም በ2018 በጀት ዓመት በርካታ የኃይል መሠረተ ልማት ፕሮጀክቶችን፣ የኦፕሬሽንና የጥገና ሥራዎችን በመሥራት ተቋማዊ የመፈጸም አቅምን ማላቅ መቻሉን አስታውቀዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ፣ የአሰላና የአይሻ የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች መጠናቀቅ ኃይል የማመንጨት አቅምን ወደ 9 ሺህ 730 ሜጋ ዋት በማሳደግ የ23 በመቶ ዕድገት እንዲመዘገብ ማስቻሉን ተናግረዋል።

በተጠናቀቀው በጀት ዓመትም ጠቅላላ የኃይል ምርት አቅም 35 ሺህ 671 ጊጋ ዋት በሰዓት በማድረስ የ124 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ገቢ ማግኘት እንደተቻለ አስረድተዋል።

ከኃይል ሽያጭና ዳታ ማይኒንግ 475 ነጥብ 7 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ መገኘቱም የተቋሙን የገቢ አቅም ከባለፈው በጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ64 በመቶ ዕድገት እንዲመዘገብ አስችሏል ብለዋል።

በአጠቃላይ በበጀት ዓመቱ 39 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ በማስመዝገብ ተቋሙ ለመጀመሪያ ጊዜ ከዕዳ ወደ ትርፋማነት የተሸጋገረበትን ስኬታማ ዘመን እንዳሳለፈ ጠቅሰዋል።

በዚህም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ከነበረበት ዕዳ ተላቆ ወደ ውጤታማ የትርፋማነት ምዕራፍ መሸጋገሩን አብስረዋል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ላስመዘገበው ስኬትም የተቋሙ አመራር፣ ሠራተኞችና ባለድርሻ አካላት ሚና የላቀ መሆኑን በማንሣት ለዚህ ሁሉንም አመስግነዋል።

ጳጉሜን 4 ቀን 2017 ዓ.ም የሁሉም ዜጎች ኩራትና አሻራ ያረፈበት ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ተጠናቆ በይፋ የተመረቀበት ታሪካዊ ዕለት መሆኑንም አስታውሰዋል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የተቋም ቀንም የሕዳሴን ታሪካዊ ፍጻሜ በመዘከር የላቀ አፈጻጸም ለነበራቸው አመራርና ሠራተኞች ዕውቅና ለመስጠት ያለመ መሆኑን ገልጸዋል።

በቀጣይም በየዓመቱ ጳጉሜን 4 የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የተቋም ቀን ሆኖ እንደሚከበር አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም