ቀጥታ፡

በአብሮነትና በተደመረ አቅም ወገኖችን ማገዝ፣ ትውልድን መገንባትና ሀገርን ማፅናት እንደሚቻል በተግባር እየታየ ነው

ሠመራ፤ ጳጉሜ 4/2018 (ኢዜአ)፦ በአብሮነትና በተደመረ አቅም ወገኖችን ማገዝ፣ ትውልድን መገንባትና ሀገርን ማፅናት እንደሚቻል በተግባር እየታየ መሆኑን የአፋር ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ኡመር ኑር ገለጹ።

ጳጉሜን 4 "የሕብር ቀን" "ብዝሃነት የኢትዮጵያ ጌጥ" በሚል መሪ ሃሳብ በአፋር ክልል ሠመራ ከተማ በጎ ተግባራትና ድጋፍ በማድረግ ተከብሯል።

መርሃ ግብሩ የደም ልገሳ በማድረግ፣ የትምህርት ቁሳቁስና ሌሎችም ድጋፎች እንዲሁም በዱብቲ አጠቃላይ ሆስፒታል ታካሚዎችን በመጠየቅ፣ ማዕድ ማጋራትና ነፃ የሕክምና አገልግሎት መስጠት ተችሏል።


 

በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የአፋር ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድና የመሬት ቢሮ ኃላፊ ኡመር ኑር፤ እለቱን በሰብአዊነትና መልካም ተግባራትን በማከናወን ማክበር መቻሉ ሁላችንንም ያስደሰተ ተግባር ነው ብለዋል። 

በአብሮነትና በተደመረ አቅም ወገኖችን ማገዝ፣ ትውልድን መገንባትና ሀገርን ማፅናት እንደሚቻል በተግባር እየታየ መሆኑን ገልጸዋል።

በዛሬው እለትም የተከናወነው ተግባር የዚሁ ማሳያ መሆኑን አንስተው መሰል ተግባራት ባህል ሆነው መቀጠል አለባቸው ብለዋል።

የክልሉ መንግሥት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ መሐመድ ዓሊ፤ የኢትዮጵያዊያን የመተጋገዝ፣ መረዳዳትና አብሮነትን የማጠናከር ተግባር ባህል ሆኖ መቀጠሉን አንስተዋል።

በዚሁ መሰረት የህብር ቀንን ምክንያት በማድረግ በአፋር ክልል የተለያዩ በጎ ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸው በሰመራ ከተማ የታመሙ ወገኖችን በመጠየቅ፣ ድጋፍ በማድረግና ደም በመለገስ መከበሩን ተናግረዋል።


 

በእለቱ የችግኝ ተከላ፣ የደም ልገሳ፣ የትምህርት ቁሳቁስና የንጽህና መጠበቂያ ድጋፍ እንዲሁም በዱብቲ አጠቃላይ ሆስፒታል ታካሚዎችን በመጠየቅ ማእድ ማጋራት ተችሏል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም