የሕብር ቀን ሕብረ ብሔራዊ አንድነትና የአብሮነት እሴቶችን ለማጠናከር አይነተኛ ድርሻ አለው - ከንቲባ ከድር ጁሃር - ኢዜአ አማርኛ
የሕብር ቀን ሕብረ ብሔራዊ አንድነትና የአብሮነት እሴቶችን ለማጠናከር አይነተኛ ድርሻ አለው - ከንቲባ ከድር ጁሃር
ድሬዳዋ፣ ጳጉሜን 4/2018 (ኢዜአ)፡-የሕብር ቀን ሕብረ ብሔራዊ አንድነትና የአብሮነት እሴቶችን ለማጠናከር አይነተኛ ድርሻ ማበርከቱን የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር ገለጹ።
በድሬዳዋ ጳግሜን-4 "የሕብር ቀን" ህብረ ብሔራዊ አንድነትን በሚያስቀጥሉ የበጎ ተግባራት ሥራዎች ተከብሯል።
ቀኑን ምክንያት በማድረግ ለተቸገሩ ወገኖችና፣ ለተማሪዎች እንዲሁም ለመቄዶኒያ የአረጋዊያን መርጃ ማዕከል ድጋፍ ተደርጓል።
የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር በወቅቱ እንዳሉት የሕብር ቀን መከበር ሕብረ ብሔራዊ አንድነትና የአብሮነት እሴቶችን ለማጠናከር አይነተኛ ድርሻ አለው።
አስተዳደሩ የአብሮነትና የእርስ በርስ መረዳዳት እሴቶችን በማጠናከር ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማትን ለማሳካት አበክሮ ሲሰራ መቆየቱንም ጠቁመዋል።
በተለይም የአብሮነትና የአንድነት እሴቶችን በማጠናከርና ሰው ተኮር ልማትን በማስፋፋት ማህበራዊ ኃላፊነቶችን መወጣት ላይ ትኩረት መሰጠቱን ተናግረዋል።
በቀጣይም ይህን መልካም ተግባር በማስቀጠል ለትውልድ የምትመች ሀገርን ለማስረከብ በጋር መስራት ይገባል ብለዋል።
የድሬዳዋ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሱልጣን አልይ በበኩላቸው ብዝሀነት ለልዩነት ሳይሆን በጋራ ለማደግ መሰረት መሆኑን ተናግረዋል።
ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን ይበልጥ ለማጠናከር የጋራ ትርክት ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ገልጸው፣ የሕብር ቀን መከበሩ የህብረተሰቡን አብሮነት ለማጎልበት ያግዛል ብለዋል።
በተለይ ቀኑን ምክንያት በማድረግ የህብረተሰቡን የመረዳዳት እሴቶች በመተግበር ለችግር የተጋለጡ ወገኖችን መርዳት መጀመሩ የሚበረታታ መሆኑን ተናግረዋል።
በመርሀ ግብሩ ላይ የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አብዲ ሙክታርን ጨምሮ የአስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮችም ተሳታፊ ሆነዋል።