ቀጥታ፡

የእስያ መሰረተ ልማት ኢንቨስትመንት ባንክ የኢትዮጵያን የመሰረተ ልማት ስራዎች ለመደገፍ ያለውን ቁርጠኝነት አረጋገጠ

አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 4/2018 (ኢዜአ):- የእስያ መሰረተ ልማት ኢንቨስትመንት ባንክ የኢትዮጵያን የመሰረተ ልማት አጀንዳዎች እንደሚደግፍ አስታወቀ።

የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ አዲሷን የእስያ መሠረተ ልማት ኢንቨስትመንት ባንክ (AIIB) ፕሬዝዳንት ዙ ጂያዪን ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

በውይይቱ ላይ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው ተሳትፈዋል።



የሁለቱ ወገኖች ውይይት ባንኩ በቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ላይ ሊኖረው የሚችለውን ተሳትፎ ጨምሮ በአበይት የኢትዮጵያ የልማት ትኩረቶች ላይ ያተኮረ ነው።

ከዚህም ባሻገር በኢነርጂ ዘርፍ እና የአየር ንብረት ለውጥን በሚከላከሉ ፕሮጀክቶች ዙሪያ ያላቸውን አጋርነት ማሳደግ፣ በዝቅተኛ ወለድ የሚሰጡ የብድር አቅርቦቶችን ማመቻቸት እንዲሁም ከሌሎች ባለብዙ ወገን የልማት ባንኮች ጋር በቅንጅት መሥራት በሚቻልበት ሁኔታ ላይም መክረዋል።

በውይይቱ ወቅት የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ ለፕሬዝዳንት ዙ ጂያዪ የኢትዮጵያ ሪፎርም አጀንዳ አፈጻጸም እና እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ያሉ ግዙፍ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ ረገድ የተመዘገቡ ስኬቶችን አስመልክቶ ገለጻ አድርገዋል።

ሚኒስትሩ አክለውም ባንኩ ኢትዮጵያ ቅድሚያ የምትሰጣቸውን የልማት ትኩረቶች መደገፍ የሚችልባቸውን የፋይናንስ አማራጮች አቅርበዋል።

ፕሬዝዳንት ዙ ጂያዪ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በቀጣናው የኃይል ትስስርን በማስፋት ረገድ እየተወጣች ያለውን ግንባር ቀደም ሚና አድንቀዋል።

ባንኩ የኢትዮጵያን የመሰረተ ልማት አጀንዳ ለመደገፍ ያለውን ቁርጠኝነትም አረጋግጠዋል።

ሁለቱ ወገኖች አጋርነታቸውን በማጎልበት፤ ዘላቂና አሳታፊ የመሰረተ ልማት ዕድገትን በጋራ እውን ለማድረግ ቁርጠኝነታቸውን ገልጸዋል።

የእስያ መሠረተ ልማት ኢንቨስትመንት ባንክ (AIIB) ፕሬዝዳንት ዙ ጂያዪ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ይፋዊ የስራ ጉብኝት እያደረጉ እንደሚገኝ የገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም