በኦሮሚያ ክልል ከ2ሺህ 700 በላይ የሕግ ታራሚዎች በይቅርታ እንዲፈቱ ተወሰነ - ኢዜአ አማርኛ
በኦሮሚያ ክልል ከ2ሺህ 700 በላይ የሕግ ታራሚዎች በይቅርታ እንዲፈቱ ተወሰነ
አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 4/2018 (ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል 2 ሺህ 735 የሕግ ታራሚዎች በይቅርታ እንዲፈቱ መወሰኑን የኦሮሚያ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ቢሮ ኃላፊ ጉዮ ዋርዮ ገለጹ።
በይቅርታ የተፈቱ ታራሚዎቹ 2ሺህ 518 ወንዶች እና 217 ሴቶች መሆናቸውን ኃላፊው በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል።
የይቅርታ ሂደቱ በክልሉ ሕገ መንግሥት ለፕሬዚዳንቱ በተሰጠው ሥልጣን እና በይቅርታ መመሪያ ቁጥር 10/2013 መሠረት መከናወኑን ገልጸዋል።
በመመሪያው መሠረት ከ3 ወር ቀላል እስራት እስከ 25 ዓመት ጽኑ እስራት የተፈረደባቸውና ከተወሰነባቸው የእስራት ጊዜ አንድ ሦስተኛውን ወይም ከዚያ በላይ ያሳለፉ ታራሚዎች የይቅርታ መስፈርቱን ሊያሟሉ ይችላሉ ብለዋል።
ታራሚዎች ለይቅርታ ብቁ መሆናቸው ሲጣራ በማረሚያ ቤት ያሳዩት ሥነ-ምግባር፣ ከተፈረደባቸው ጊዜ ያሳለፉት የእስራት ጊዜ እና የጉዳያቸው የመጨረሻ ውሳኔ መኖሩ እንደሚታዩ ተናግረዋል።
በተጨማሪም የሞት ቅጣት የተፈረደባቸው፣ ተደጋጋሚ ወንጀል የፈጸሙ እና በይቅርታ ከተፈቱ በኋላ ሌላ ወንጀል የፈጸሙ ታራሚዎች እንደማይካተቱ ገልጸዋል።
የይቅርታ አሰጣጡ ዋና ዓላማ የማኅበረሰቡን ሰላምና ጥቅም ማስጠበቅ እና ታራሚዎች ከተፈቱ በኋላ ወደ ማኅበረሰቡ ተመልሰው ለሰላምና ልማት አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ማስቻል መሆኑን ኃላፊው ገልጸዋል።