የጳጉሜን ቀናት ህዝባችንን በሚያሰባስቡ፣ አንድነትን በማጠናከርና እርስ በእርስ በመደጋገፍ ማሳለፍ ህብረ ብሔራዊ አብሮነትን ያጠናክራል - ኢዜአ አማርኛ
የጳጉሜን ቀናት ህዝባችንን በሚያሰባስቡ፣ አንድነትን በማጠናከርና እርስ በእርስ በመደጋገፍ ማሳለፍ ህብረ ብሔራዊ አብሮነትን ያጠናክራል
አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 4 /2018 (ኢዜአ)፦የጳጉሜን ቀናት ህዝባችንን በሚያሰባስቡ፣ አንድነትን በሚያጠናክሩና እርስ በእርስ በመደጋገፍ ማሳለፍ ተስፋንና ህብረ ብሔራዊ አብሮነትን እንደሚያጠናክር የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ከይረዲን ተዘራ (ዶ/ር) ገለጹ።
የሰላም ሚኒስቴር የጳጉሜን ወር "የሕብር ቀን"ን ምክንያት በማድረግ የሃይማኖት አባቶችን፣ የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አመራሮችን፣ የሲቪክ ማህበራት ተወካዮችንና የተቋሙን ሰራተኞች ያሳተፈ የመስክ ጉዞ መርሃ-ግብር አካሂዷል።
በመድረኩ የተገኙት የሰላም ሚኒስትር ዴኤታው፣ ህብረ ብሔራዊ አንድነታችንን በማጠናከር ጠንካራ ሀገራዊ አቅምን ለመፍጠር የመደመር መንግስት በትኩረት እንደሚሰራ አብራርተዋል።
የኢትዮጵያውያን መገለጫ የሆኑትን የሃይማኖትና የቋንቋ ብዝሃነት እንደ ሀገራዊ እምቅ አቅም በመጠቀም ጠንካራ አብሮነትን ለመፍጠር የተጀመሩ ሥራዎች ውጤታማ ናቸው ብለዋል፡፡
ብዝሃነት የኢትዮጵያውያን መገለጫ በመሆኑ፣ በቀጣይም ይህን ሕብር ለሀገር ጠንካራ መሰረት ለማድረግ የሚያስችሉ በርካታ ስራዎች ታቅደው እየተከናወኑ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።
በተጨማሪም የተካሄደው ሀገራዊ ምክክር የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካና የማህበራዊ ጥያቄዎችን በሰላማዊ መንገድ መመለስ የሚያስችል አቅም ያሳየ ትልቅ ጉባኤ እንደነበር ገልጸዋል።
መጪው የ2019 አዲስ ዓመት ሀገራዊ አንድነት የሚጠናከርበት፣ ታላላቅ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው የህዝብ ተጠቃሚነት የሚረጋገጥበትና የብልጽግና ዘመን እንዲሆን ተመኝተዋል።
የሃይማኖት አባቶች በጸሎታቸው፣ ሰራተኞች ደግሞ ባላቸው አቅም ሁሉ ጠንክረው በመስራት በግለሰብ፣ በቤተሰብና በማህበረሰብ ደረጃ ያሉ ስኬቶችን እንዲያስቀጥሉ አሳስበዋል።
አዲሱን ዓመት በይቅርታ፣ በውይይትና በአንድነት ለመጀመር የሚደረጉ መሰል ጉዞዎች በማህበረሰቡ ዘንድ አዎንታዊ ተስፋንና አብሮነትን ያጠናክራሉ ብለዋል።