ቀጥታ፡

የኢትዮጵያውያን ሀገር በቀል የግጭት አፈታት ሥርዓቶች ለዘላቂ ሰላምና የህዝብ አብሮነት ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ናቸው

አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 4 /2018 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያውያን ሀገር በቀል የግጭት አፈታት ሥርዓቶች ለዘላቂ ሰላምና የህዝብ አብሮነት ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆናቸውን የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ገለጹ።

የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በሕብር ያሸበረቁ የቋንቋ፣ የሃይማኖት፣ የባህልና ሌሎች ውብ መገለጫዎች አብሮነትና አንድነትን በማጎልበትም ጉልህ ሚና የሚጫወቱ ናቸው።

ይህም የኢትዮጵያውያን በሕብረ ብሔራዊ አንድነት ያሸበረቁ ጌጦቻቸውን በመጠቀም የሀገራቸውን ዳር ድንበርና ሉዓላዊ አንድነት በማስክበር ለሺህ ዘመናት ዘልቀዋል።

የገዳ ሥርዓት፣ ሽምግልና፣ አፊኔና መሰል ሀገር በቀል ኢትዮጵዊያን እሴቶችም በዜጎች መካከል የሚከሰቱ ግጭቶችን በመፍታት በሀገር ግንባታ ሂደት ጉልህ ሚና እያበረከቱ ይገኛል።

በነሐሴ 30/2018 ዓ.ም የሰላም ሚኒስቴር በደብረ ማርቆስ ከተማ ባዘጋጀው የሰላም ግንባታ፣ የባህላዊ ሃብቶችና ሀገር በቀል ዕውቀቶች የክልሎች ልምድ ልውውጥ የምክክር መድረክ ማካሄዱ ይታወሳል።

የመድረኩ ተሳታፊ የክልል ተወካይ የኃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና የኦሮሞ አባገዳዎች ለኢዜአ እንዳሉት፤ ሀገር በቀል እሴቶች ለግጭት አፈታት ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው።

ከአማራ ክልል የተወከሉት የመድረኩ ተሳታፊ ሊቀ ካህናት ይትባረክ መኮንን እንዳሉት፤ ሰላም የሁሉም ነገር መሰረትና የፍጡራን እረፍት ነው።

ግጭት በሰው ላይ ጥቃት መፈፀም የኢትዮጵያ ባህል አይደለም፤ በፈጣሪም የተወገዘ ነው እያሉ እያስተማሩ መሆኑን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የሰላም ብርሃንና ተስፋ እየፈነጠቀ መሆኑን በመግለጽ፤ ከልጅ እስከ አዋቂ ከሊቅ እስከ ደቂቅ መልካምን በመያዝ ክፋትን መራቅ እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል።


 

የሲዳማ ሀገር ሽማግሌ ቦጋለ ወልደሃና (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ የግጭት አፈታት ሥርዓት ለዘመናት የዳበረ፣ በህብረተሰቡ ዘንድ ተቀባይነት ያለው፣ አሸናፊና ተሸናፊ የሌለው ሀገር በቀል እሴቶች መኖራቸውን ገልጸዋል።

በሲዳማ ክልል አፊኔ የባህላዊ ግጭት መፍቻ ሥርዓት መሆኑን ጠቅሰው፤ መንግሥት ለህዝቦች አንድነትና አብሮነት መሰረት የሆኑ ባህላዊ እሴቶችን ጠብቆ ለማቆየት አስደናቂ ጥረት እያደረገ መሆኑን አንስተዋል።

የጋምቤላ ክልል ሀገር ሽማግሌ ጆን ዋኙ፤ በጋምቤላ ክልል በሁለት ቡድኖች አልያም ግለሶቦች መካከል የሚከሰቱ ግጭቶችን በባህላዊ እሴት መፍትሔ በመስጠት ዘላቂነት እርቅ እንደሚፈጸም ገልጸዋል።


 

የድሬዳዋ ሀገር ሽማግሌ ጉልላት ደምሴ፤ የሀገር ሽማግሌ የእያንዳንዱ ዜጋ ቤተሰብ የፍትህ አባት ተደርጎ ይቆጠራል ብለዋል።

ለአብነት የጋሞ አባቶች የተበሳጩ ወጣቶችን በቀጤማ የመለሱበት መንገድ ኢትዮጵያውያን በሀገር ሽማግሌዎች ላይ ያላቸውን ጥብቅ እምነት እንደሚያሳይ ገልጸዋል።


 

በቀጣይም የሁሉም ክልሎች የሀገር ሽማግሌዎችና የሀይማኖት አባቶች ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና አብሮነት የሚጠቅም የፍትህ አገልግሎት እንዲሰጡ ጥሪ አቅርበዋል።

የጋሞ ሀገር ሽማግሌ ሰዲቃ ሰሜ፤ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ወጣቶች በአስተውሎት በመራመድ ችግሮችን በውይይትና በሃሳብ የበላይነት የመፍታት ልምድን ማዳበር አለባቸው ብለዋል።


 

ለዚህ ደግሞ የኢትዮጵያ እሴት የሆነው የጋሞ ባህላዊ የግጭት አፈታትና ዕርቅ ሥርዓት ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል።

የኦሮሞ አባ ገዳ ጫላ ሶሪ በበኩላቸው፤ ግጭቶች እንዳይፈጠሩ ማስተማር ቅድሚያ ሰጥተው የሚሰሩበት እንደሆነ ገልጸዋል።


 

በዜጎችና ቡድኖች መካከል የሚከሰቱ ግችቶችንም በገዳ የግጭት አፈታት ሥርዓትና እሴት መሰረት ለሺህ ዘመናት በሽምግልና የዕርቅ ሥርዓት እንዲፈቱ እየተደረገ እንደመጣ ተናግረዋል።

በኦሮሞ የገዳ ሥርዓት ግጭቱ ዳግም እንዳያገረሽ ተደርጎ እንደሚፈታ በመጥቀስ፤ ለበቀል የሚነሳ ካለ ማህበራዊ አገልግሎት ይገለላል ብለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም