የዲጂታል ኢኮኖሚና መሰረተ ልማትን በማስፋት አንድነትንና ልማትን የሚያጠናክር ነገን እየገነባን ነው - ኢዜአ አማርኛ
የዲጂታል ኢኮኖሚና መሰረተ ልማትን በማስፋት አንድነትንና ልማትን የሚያጠናክር ነገን እየገነባን ነው
አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 4 /2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያን የዲጂታል ኢኮኖሚና መሰረተ ልማት በማስፋት አንድነትና ልማትን የሚያጠናክር አውድ መፍጠር የሚያስችል ነገን እየገነባን ነው ሲሉ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ገለጹ።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከሌሎች የፌዴራል ተቋማት ጋር በመተባበር ነገ ጳጉሜን 5 ቀን 2018 ዓ.ም የሚከብረውን የ"ነገ ቀን" በማስመልከት መግለጫ ሰጥቷል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ መንግሥት የጳጉሜን ቀናት በተለያዩ ስያሜዎች እያከበረ ይገኛል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከሌሎች ተቋማት ጋር በመተባበር በዲጂታል ኢኮኖሚ የዳበረች ኢትዮጵያን ለማስረከብ የሚከናወኑ ተግባራትን የሚያሳየው የነገ ቀን ይከበራል ብለዋል።
ኢትዮጵያ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎችን በመቅረጽ የዲጂታል ኢኮኖሚ መገንባት የሚያስችል ሥራ እያከናወነች መሆኑን ገልጸዋል።
በዲጂታል ቴክኖሎጂ አቅም የጎለበተ፣ ዘመኑን የዋጀ ሲቪል ሰርቪስ በመገንባት፣ ፈጣንና ቀልጣፋ የመንግሥት አገልግሎት በመስጠት ምን ዓይነት ነገን እንገንባ በሚለው ላይ መሠረት እየጣልን ነው ብለዋል።
ነገ ማለት ወጣቶች የሚረከቧት ኢትዮጵያ ማለት ነው ያሉት ሚኒስትሩ፤ ለትውልዱ የአንድነት፣ የሰላምና የልማት አውድ መፍጠር የሚያስችል ነገን ለመገንባት መሆኑን ገልጸዋል።
አዲስ ዓመት አዲስ ተስፋና ሀሳብ መፈጠሪያ መሆኑን ገልጸው፤ ለሕዝባችን የገባነውን ቃል በተግባር መፈጸም ይገባናል ብለዋል።
አዲሱ ዓመት ፈተናዎችን አልፈን የተሳካ ሰላምና ልማት የምናስመዘግብበት እንዲሆን እመኛለሁ ብለዋል።