ቀጥታ፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ባበረከቱልን የበዓልና የትምህርት ቁሳቁስ ስጦታ ተደስተናል

አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 4/2018 (ኢዜአ)፦ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ባበረከቱላቸው ለአዲስ ዓመት በዓል መዋያና የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ መደሰታቸውን ስጦታው የተበረከተላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መጪውን የ2019 ዓ.ም የኢትዮጵያ አዲስ ዓመት በዓልን አስመልክቶ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ሠራተኞች የበዓል ስጦታ እንዲሁም በጽሕፈት ቤቱ ድጋፍ ለሚያድጉ ሕፃናት የትምህርት መርጃ ቁሳቁስ አበርክተዋል።


 

ስጦታ ከተበረከተላቸው መካከል  አዲስ ሳህሌ እንዳሉት፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያበረከቱላቸው ስጦታ በዓሉን በደስታ እንዲያሳልፉ የሚያደርጋቸው መሆኑን ገልጸዋል።

ለልጆቻቸው የተበረከተላቸው የትምህርት መርጃ ቁሳቁስም በቀጣዩ የትምህርት ዘመን ያለአንዳች ጭንቀት ትምህርታቸውን የሚከታተሉበት ዕድል እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል።

ላደረጉት የበዓል መዋያና የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።


 

ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ ወይዘሮ ሞቱ ቶለሳ በበኩላቸው፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በበዓላት ወቅት የሚያደርጉት ድጋፍ የመረዳዳትና የእርስ በእርስ መተሳሰብ ባህልን እያጎለበተ መሆኑን ገልጸዋል።

የተደረገላቸው ስጦታ በዓሉን በደስታ በማሳለፍ ልጆቻቸው ሙሉ ተስፋና ዝግጅት ሰንቀው ወደ ትምህርት ቤት እንዲሄዱ የሚያስችላቸው መሆኑንም አብራርተዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ድጋፍ ከሚያድጉ ተማሪዎች መካከል ተማሪ እቴነሽ ዓለሙ በበኩሏ፤ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ስጦታ በዓሉን ከቤተሰቧ ጋር በታላቅ ደስታ እንድታሳልፍ እና የትምህርት መርጃ ቁሳቁስ እንድታገኝ ዕድል የፈጠረላት መሆኑን ገልጻለች።


 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ያበረከቱላት የትምህርት መርጃ ቁሳቁስ በቀጣዩ የትምህርት ዘመን ትምህርቷን ያለ አንዳች ችግርና ስጋት እንድትከታተል የሚያስችላት መሆኑንም ተናግራለች።

በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በየጊዜው ለሚያደርጉላቸው የበዓል መዋያና የትምህርት መርጃ ቁሳቁስ ድጋፍ ልባዊ ምስጋናዋን አቅርባለች።


 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ሁል ጊዜም ለበዓል መዋያ ለሚያደርጉላቸው ድጋፍ ምስጋና ያቀረቡት ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ ወይዘሮ ትናኝ አየነው ናቸው።


 

ሌላኛዋ ስጦታ ከተበረከተላቸው መካከል ወይዘሮ እመቤት ሶሪ በበኩላቸው፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያበረከቱላቸው ድጋፍ ልጃቸው በቀጣዩ የትምህርት ዘመን ትምህርቱን ያለ አንዳች ችግርና ስጋት የሚከታተልበትን ምቹ ዕድል የፈጠረለት መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም