ቀጥታ፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የጥቁር ሕዝቦች የመቻል ተምሳሌት 

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የጥቁር ሕዝቦች የመቻል ተምሳሌት 

መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም የኢትዮጵያውያን የጋራ ቃል ኪዳን የታሰረባት ታሪካዊ ክስተት ናት። ዕለቷም የዓባይን የሺሕ ዘመናት ገደብ የሌለው ጉዞ በጉባ ተራሮች ግርጌ ልጓም ለማበጀት የታሰረች ቀለበት ሆና ተመዝግባለች።

ኢትዮጵያውያን ቃል ኪዳናቸውን ባሰሩ ማግስት የግብፅና ሌሎች ታሪካዊ የኢትዮጵያ ጠላቶች ጩኸትና የጥፋት ሴራ በግልጽ መታየት ጀመረ። በተለይም ግብፅ ኢትዮጵያ ውስጣዊ መረጋጋት እንዳይኖራት የውስጥ ታጣቂዎችን ከመደገፍ ጀምሮ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በራፍ ጭምር የሀሰት ክሶችን እስከማሰማት የደረሰ የሺሕ ዘመናት ዓባይን በብቸኝነት የመጠቀም አባዜዋን አንጸባርቃለች።

ትብብርን ከፅናት አሰናስለው የቀጠሉት ኢትዮጵያውያን ለአሥራ አራት ዓመታት የታላቁ ሕዳሴ ግድብን የማደናቀፍ የታሪካዊ ጠላቶችን ሴራ በጋራ በመመከት ለፍጻሜ አብቅተውታል። የሀገርን ሉዓላዊነት በጽናት የማስከበር የአርበኝነት ተጋድሎን ከዓድዋ ጀግኖች የወረስን እኛ ኢትዮጵያውያን በጉባ ተራሮች ግርጌ በደም፣ በላብ፣ በዕንባና በውኃ ጠብታ ታላቁ የሕዳሴ ግድብን በዓባይ ላይ አንጸናል።


 

ጳጉሜን 4 ቀን 2017 ዓ.ም የአዲስ ዓመት ዋዜማም ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን በማጠናቀቅ ለፍጻሜ በማድረስ አብስሯል። ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሺሕ ዘመናት የልማት ጥማትን በማርካት የብልፅግና ፍኖት ብስራት ሆኗል።

ታላቁ ሕዳሴ ግድብ ለሌላ የልማት ዕቅድ ወጋገን የፈነጠቀ የንጋት ሐይቅ ፈጥሯል። ግድቡ በኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝቦቿ ትብብር ብቻ ያለ አንዳች የውጭ ድጋፍና ብድር ለፍጻሜ መብቃቱም ለአፍሪካውያን የመቻል ትዕምርት ሆኗል። በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ብስራት በጉባ ተራሮች ግርጌ የከተሙ የምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ሀገራት መሪዎች የመሰከሩት ጥሬ ሐቅም ይህ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በምረቃው ዕለት እንደገለጹት፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የጥቁር ሕዝቦችን የታሪክ ክብር ያደሰና ለአፍሪካውያን የመቻል ውጤት ነው። 

በወቅቱም የታላቁ ሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያን የብልፅግና ጎህ ያበሰረ፣ ቀጣናዊ የኃይል ትስስርና የጋራ ዕድገት መንገድ የጠረገ ፓን-አፍሪካኒዝም ፕሮጀክት መሆኑን መግለጻቸው ይታወሳል። የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቅ አፍሪካውያን አንጡራ ሀብታቸውን በራሳቸው አቅምና ጥረት በማልማት ታላላቅ የልማት ገድሎችን መፈጸም እንደሚችሉ ያመላከተ የጥቁር ሕዝቦች ሁሉ የኩራት ምንጭ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር እና የክብር እንግዳ መሐሙድ አሊ ዩሱፍ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ታላቁ ሕዳሴ ግድብ የታዳሽ ኃይል ሽግግርን በማፋጠን የአፍሪካውያንን የጋራ ምኞት የሚያሳካ ህያው ምልክት ነው ማለታቸው ይታወሳል።

የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቅና ለምረቃ መብቃትም የኢትዮጵያውያንን ለአንድ ሀገራዊ የልማት ርዕይ በጋራ የመቆም ውጤታማነትን በተግባር ለዓለም የገለጠ ፓን-አፍሪካኒዝም ፕሮጀክት መሆኑን መስክረዋል።

በዚሁ ወቅት የተገኙት የጅቡቲ ፕሬዚዳንት ኢስማኤል ዑመር ጌሌ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የዘመናዊው ዓለም የአፍሪካውያን የኩራት ምንጭ የሆነ የልማት ድል መሆኑንና መላውን ዓለም ያስደነቀ የኢትዮጵያ ስኬትና የወዳጆቿ የጋራ ሀብት ነው።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ብሔራዊ ፕሮጀክት ብቻ ሳይሆን አስደማሚ የፓን-አፍሪካኒዝም መግለጫ ፕሮጀክት ነው ያሉት ደግሞ በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ምረቃ ላይ የታደሙት የኬንያው ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ ናቸው።


 

የኢትዮጵያውያን ብሔራዊ ፕሮጀክት የሆነው የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ስኬት አፍሪካውያን በተባበረ ክንድ አቅማቸውን በመጠቀም የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው መወሰን እንደሚችሉ ትምህርት ያስተላለፈ ነው ሲሉም መግለጻቸው ይታወሳል። 

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ የምህንድስና ልህቀትም አህጉሪቱ ለብልፅግናዋ የሚረዱና ሁለንተናዊ ለውጥ የሚያመጡ ሁነኛ የልማት ፕሮጀክቶችን በራሷ አቅም የመገንባት ብቃት እንዳላት ማረጋገጫ ነው።

በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ምረቃ ላይ የተገኙት የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሃሙድ እንደተናገሩት፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ አህጉራዊ ትብብርና ግንኙነትን የሚያጠናክር የወንድማማችነት ምልክት ነው።

ፕሬዝዳንቱ አክለውም ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሁላችንንም ተጠቃሚ የሚያደርግ የጋራ ጉዳያችን ነው በዚህም ዕድለኞች ነን ሲሉ መግለጻቸውም ይታወሳል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ "ለእኛ እንደ አንድ ፕሮጀክት ሳይሆን ሀላፊነትን የምንጋራበት ነው" ያሉት ፕሬዝዳንቱ አፍሪካውያን ከተባበርን ስኬቶችን ማስመዝገብ እንደምንችል ትልቅ ማሳያ ነው ብለዋል።

የላይኛውና የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት መበልጸግ የሚችሉት በጋራ እንደ አንድ ማህበረሰብ በመስራት ነው። ውሃና ሌሎች ተፈጥሯዊ ሀብቶች በድንበር የተወሰኑ ሳይሆኑ የወደፊት እጣ ፈንታችንን የሚወስኑ ናቸው ብለዋል።


 

የደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት ሳልቫኪር ማያርዲት በበኩላችው እንደሚሉት፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የአንድነት እና የመስዋዕትነት ምልክት ነው። ግድቡ ፕሮጀክት ብቻ ሳይሆን የአንድነትና የመስዋዕትነት ምልክት ነው፡፡

የግድቡ ግንባታ እውን መሆን ህዝብ ከተባበረ እና ለአንድ ዓላማ በአንድነት ከቆመ ምን መስራት እንደሚችል ማሳያ መሆኑን ነው ያነሱት ፕሬዝዳንቱ፤ ይህም ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ የኩራት ምንጭ ነው ማለታቸው ይታወሳል።

ፕሬዝዳንቱ አክለውም ግድቡ የኃይል ፍላጎትን ከማሳካት ባለፈ ለልጆቻችን የምንመኘውን የበለጸገ ሀገርና አህጉር ለማስረከብ እድል የሚፈጥር ነው ብለዋል።

ይህ በታሪክ ድርሳናት ሰፊውን ድርሻ የሚይዘው የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ስኬት የኢትዮጵያዊያን የቃል ኪዳናቸው ማህተም ሆኖ ለዘላለም ይኖራል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም