ኢትዮጵያ በሰው ሰራሽ አስተውሎት እያከናወነች ያለችው ውጤታማ ተግባር ለቀጣናው የዲጂታል ትብብር በተሞክሮነት የሚጠቀስ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በሰው ሰራሽ አስተውሎት እያከናወነች ያለችው ውጤታማ ተግባር ለቀጣናው የዲጂታል ትብብር በተሞክሮነት የሚጠቀስ ነው
አዲስ አበባ፤ጳጉሜን 4 /2018 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በሰው ሰራሽ አስተውሎት፣ በሳይበርና መረጃ ደህንነት እያከናወነች ያለችው ውጤታማ ተግባር ለቀጣናው የዲጂታል ትብብር በተሞክሮነት የሚጠቀስ መሆኑን የምስራቅ አፍሪካ መንግሥታት በይነ-መንግሥታዊ ባለሥልጣን (ኢጋድ) ገለጸ።
የኢጋድ የኢኮኖሚ ትብብርና ቀጣናዊ ውህደት ዳይሬክተር ሙሂየልዲን አልቶሃሚ ጠሃ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ በሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) እና በቴክኖሎጂ ዘርፍ ያካበተችው ተሞክሮ ለኢጋድ አባል ሀገራት የተሻለ ትምህርት የሚሰጥ ነው።
በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ባደረጉት ጉብኝት በሳይበር ደህንነት፣ በዳታ ጥበቃና በሰው ሰራሽ አስተውሎት ዘርፍ የተከናወኑ ተግባራት ለቀጣናዊ የእውቀት ሽግግር ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳላቸው መገንዘባቸውን ተናግረዋል።
ኢጋድ በአሁኑ ወቅት እያዘጋጀው የሚገኘው የሰው ሰራሽ አስተውሎት ማዕቀፍ የአባል ሀገራትን የዘርፉ ፖሊሲ፣ የመረጃ ጥበቃና የአጠቃቀም ሥነ-ምግባር፣ ተቋማዊ አቅም፣ የሰው ኃይል ልማትና የእውቀት ሽግግር ላይ አተኩሮ እንደሚሠራ አስረድተዋል።
የኢጋድ አባል ሀገራት በዘርፉ ያለባቸውን የአቅም ክፍተት ለመሙላትና ቀጣናዊ ልማትን ለማፋጠን እንደ ኢትዮጵያ የተሻለ አቅም ካላቸውና ውጤታማ ተግባር እያከናወኑ ከሚገኙ ሀገራት ልምድና ተሞክሮ መውሰድ እንዳለባቸው አሳስበዋል።
ሰው ሰራሽ አስተውሎት በቀጣናው በተለይም በግብርና፣ በጤና፣ በትምህርት እንዲሁም በሰላምና ደህንነት ዘርፎች የሚከናወኑ የልማት ተግባራትን ለማገዝ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው አመልክተዋል።
የቴክኖሎጂውን ጥቅም በስፋት ለማጎልበት የሰው ኃይል ልማትን ማጠናከር፣ ቀጣናዊ ትብብርን ማሳደግና የእውቀት ሽግግር ማድረግ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
የቴክኖሎጂ ባለሙያው ሰለሞን ካሳ በበኩሉ፤ የሰው ሰራሽ አስተውሎት እንደ ጤና እና ግብርና ያሉ ዘርፎችን ለመደገፍ ብሎም እንደ ድርቅ ያሉ ተፈጥሯዊ አደጋዎችን አስቀድሞ በመተንበይ ምርታማነትና ዕድገትን እንደሚያፋጥን ገልጿል።
ኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲቲዩት በማቋቋም፣ ፖሊሲ በመንደፍ እና ምርምሮችን በማካሄድ ለአጎራባች ሀገራት ጭምር አርዓያ የሚሆን ተግባር እያከናወነች መሆኑንም ተናግሯል።