ቀጥታ፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ እና ሀገራዊ ምክክር ጉባዔ የመቻልና የአንድነት ሕብራዊነት መገለጫዎች ናቸው

አዲስ አበባ ፤ ጳጉሜን 4/2018 (ኢዜአ) ፦ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ እና ሀገራዊ ምክክር ጉባዔ ኢትዮጵያውያን በትብብር ያሳኳቸው የመቻልና የአንድነት ሕብራዊነት መገለጫዎች መሆናቸውን የሰላም ሚኒስቴር ገለጸ። 

የሰላም ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ሃላፊ መብራቱ ካሳ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በአንድነት ማሰሪያ የተጋመዱ ናቸው።

ኢትዮጵያውያን የተጋመድን ነን ሲባል ከቃል ባለፈ በዓድዋ ጦርነትና በሌሎች ሀገራዊ ሉዓላዊነትን ለመዳፈር በተቃጡ ጥቃቶች ላይ በመተባበር በተግባር አሳይተናል ብለዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የጋራ የላብ፣ የደምና የውሃ ጠብታ ውጤት መሆኑን በመግለጽ፤ የኢትዮጵያውያን በጋራ መቻልን ያሳያል ብለዋል።

ኢትዮጵያውያን ከማንኛውም አካል ተፅዕኖ ነጻ በመሆን ራሳቸውን በራሳቸው መለወጥ ማሳደግና ማበልጸግ እንደሚችሉ ያሳዩበት የሕብራዊነት መገለጫ ነው ሲሉም ተናግረዋል።

በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባዔ በህዝቦች መካከል የዘመናት ቁርሾ ሆነው የቆዩ ልዩነቶችን በምክክር መፍታት የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያውያን የጋራ ችግራቸውን በራሳቸው አቅም በምክክር ለመፍታት ያሳዩት ቁርጠኝነት ለጠንካራ ሀገረ መንግሥት ግንባታ ያላቸውን ቀናኢነት ያሳያል ብለዋል።

ሀገራዊ ምክክር ጉባዔው ኢትዮጵያ የራሷን ችግር በራሷ እየፈታች ያለች ሀገር መሆኗን ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በተግባር ያረጋገጠ መሆኑንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም