ቀጥታ፡

የአየር ንብረት ለውጥ በማኅበረሰብ ጤና ላይ ሊያሳድር የሚችለውን ተፅዕኖ ለመከላከል የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው

አዲስ አበባ ፤ ጳጉሜን 4/2018 (ኢዜአ) ፦የአየር ንብረት ለውጥ በማኅበረሰብ ጤና እና ስነ-ምግብ ላይ ሊያሳድር የሚችለውን ተፅዕኖ ለመከላከል የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር  ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሳይ ሀይሉ ገለጹ።

የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የኢትዮጵያ አረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብር በጤና እና በስነ-ምግብ መጠበቅ ላይ ያለውን ሚና በተመለከተ የምርምር ጉባኤ የዘርፉ ተዋናዮች በተገኙበት እያካሄደ ይገኛል።

ዶክተር መሳይ ሀይሉ በመድረኩ እንደተናገሩት፤ ከተለያዩ የህብረተሰብ ጤና ፈተናዎች መካከል ከውሃ ጋር በተገናኘ የሚፈጠሩ የጤና ችግሮች እንደሚገኙበት ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዞ የሚያጋጥሙ ፈተናዎችን ለመሻገር እየወሰደቻቸው ያሉ የፖሊሲ እርምጃዎች ትልቅ ሚና አላቸው ብለዋል።

ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር በቢሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞችን መትከሏ ተስማሚ የአካባቢ አየር ንብረት እንዲኖር አድርጓል ብለዋል።

በተጨማሪም ኢትዮጵያ አረንጓዴ ትራንስፖርትን ለማበረታታት የወሰደቻቸው የፖሊሲ እርምጃዎች የአየር ብክለትን በመቆጣጠር የማኅበረሰብን ጤና ለመጠበቅና ስነ-ምግብን ለማሻሻል የራሳቸው አበርክቶ እንዳላቸው ገልጸዋል።


 

ኢንስቲትዩቱ በአረንጓዴ ልማት ላይ የሚሰሩ ስራዎችን ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ በማጥናት የደን ልማትና ንጹህ መጓጓዣ የመፍጠር እርምጃዎች ከአየር ንብረት ጋር ተያያዥነት ያላቸውን የበሽታ ጫናዎች እንደሚቀንሱ፣ የአየር ጥራትን እንደሚያሻሽሉ እና የስነ-ምግብ ክትትልን እንዴት እንደሚያጠናክሩ በጥናት የማረጋገጥ ስራ እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

ኢንስቲትዩቱ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የሚሰሩ ስራዎች በጤናው ዘርፍ ያላቸውን አበርክቶ በምርምር ስራዎች ለመፈተሽና በቀጣይ በሚሰሩ ተግባራት ላይ ከተለያዩ ተቋማት ጋር ያለውን የትብብር ስራ ለማጠናከር መድረኩ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ፈጠነ ተሾመ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ተቋሙ በመረጃ ላይ የተመሰረቱ የአየር ፀባይ ትንበያዎችን በመተንተንና በማደራጀት ለጤናው ዘርፍና ለልዩ ልዩ ጥቅሞች እንዲውሉ ተደራሽ እያደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ኢንስቲትዩቱ ከኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር የተገናኙ መረጃዎችን በመለዋወጥ የማህበረሰብ ጤና እንዲጠበቅ ትብብሩን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

ለበሽታ ክትትል፣ ለአደጋ ዝግጁነት እና ለቅድመ ማስጠንቀቂያ የሚረዱ የአየር ንብረት መረጃዎችን በወቅቱና በቀጥታ ለማድረስ ተግቶ ይሰራል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም