ቀጥታ፡

ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን በማጠናከር ለሀገር ዕድገት መትጋት ይገባል

ባህር ዳር፤ ጳጉሜ 4/2018(ኢዜአ)፦ ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን በማጠናከር ለሀገር ዕድገት መትጋት ይገባናል ሲሉ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአማራ ክልል ማህበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ/ር) ገለጹ።

በክልሉ የሚገኙ የማህበራዊ ዘርፍ ተቋማት የህብር ቀንን በባህር ዳር ከተማ በድምቀት እያከበሩ ነው።


 

የማህበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ/ር ) በመድረኩ ላይ እንደገለጹት፤ የህብር ቀን የሀገሪቱን ብዝሃነት፣ አብሮነትና አንድነት የምናስብበት ታላቅ ዕለት ነው።

ዕለቱን ስናስብ የጋራ ትርክትን በማጎልበት ለአገር እድገትና ብልጽግና በቅንጅት የመቆም ባህልን የምናጎለብትበት ነው ሲሉም አመልክተዋል።

"በጋራ ስንቆም እንበረታለን" ያሉት አስተባባሪዋ፣ አብሮነታችን ለጠላት እሳት፣ ለወዳጅ ደግሞ የብረት አጥር ለመሆን የሚያስችል ነው ብለዋል።

አክለውም ዕለቱን ስናስብ በማዳመጥ፣ በመከባበርና በመተባበር ለህብረ ብሔራዊ አንድነት መጠናከር የድርሻችንን በመወጣት መሆን አለበት ነው ያሉት።

በአዲሱ ዓመትም የተግባር ሰው በመሆን ሰላምና ልማትን በማረጋገጥ የህዝቡን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንደሚገባም አንስተዋል።

የብሔር፣ የቋንቋና የሃይማኖት ልዩነቶች ሳይገድቡ ሕብረ ብሔራዊነትን ለሀገር ግንባታ በመጠቀም መስራት እንደሚገባም ነው የተናገሩት።


 

የክልሉ ሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ብርቱካን ሲሳይ በበኩላቸው፤ ዕለቱ የብዝሃነት መገለጫና የተሰናሰለ አንድነታችን ማሳያ ነው ብለዋል።

የጳጉሜን ቀናትን ስናከብር ያለፈውን የምንገመግምበት፣ አብሮነትና የጋራ ጽናት በህብር የምናሳይበት ለቀጣይ ሥራ መነሳሳትን የፈጠረ ነው ሲሉም ተናግረዋል።

በተጨማሪም ዕለቱ ማዕድ በማጋራት፣ ደም በመለገስ፣ ነፃ ህክምና በመስጠትና ለልጆች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ በማበርከት መከበሩ ለተተኪው ትውልድ መልካም መሰረት የሚጥል መሆኑን አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም