ቀጥታ፡

በአማራ ክልል ለዘመን መለወጫ በዓል በቂ የእርድ እንስሳትና ሌሎች ምርቶች ቀርበዋል

ባህር ዳር ፤ ጳጉሜን 4/2018 (ኢዜአ) ፦ በአማራ ክልል ለዘመን መለወጫ በዓል የእርድ እንስሳትና ሌሎች ምርቶችን በበቂ መጠን ለተጠቃሚው ማቅረብ መቻሉን የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ አትክልት አሳቤ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ለዘመን መለወጫ በዓል በበቂ መጠን የእርድ እንስሳት፣ የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርቶች መቅረባቸውን ገልጸዋል።

ምርቶቹን ከኢንዱስትሪዎች፣ ከግብርና አምራቾች፣ ከኢንተርፕራይዞች፣ ከህብረት ሥራ ማህበራት እንዲሁም ከእንስሳትና አሳ ሀብት ተቋማት ጋር በመቀናጀት በተመጣጣኝ ዋጋ ለሸማቹ  ማቅረብ መቻሉን ገልጸዋል።


 

በተለይም በትላልቅ ከተሞች በተገነቡ 2ኛ ደረጃ የገበያ ማዕከላት፣ የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶችን ለሸማቹ በቀጥታ እንዲቀርብ መደረጉንም አስረድተዋል።

በበዓሉ ወቅት የምርት አቅርቦት እጥረት እንዳይኖር ቀደም ብሎ በቂ ዝግጅት በመደረጉ፣ ህብረተሰቡ በአቅራቢያው እንዲገበያይ መደረጉንም ነው ያብራሩት።

እስካሁን ባለውም ከ700 ሺህ በላይ የደለቡ ዳልጋ ከብቶች፣ በጎችና ፍየሎች እንዲሁም ከሁለት ሚሊዮን በላይ የስጋ ዶሮዎች ለበዓል ገበያ እንዲቀርቡ ተደርጓል ነው ያሉት።

በተጨማሪም ከ3 ሚሊዮን ሊትር በላይ የምግብ ዘይት፣ ከ25 ሚሊዮን በላይ እንቁላል እና ከ34 ሚሊዮን ሊትር በላይ የወተት ምርት ለገበያ ማቅረብ መቻሉን አመልክተዋል።


 

በዓሉን አስመልክቶ በሁሉም ምርቶች ላይ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ እንዳይኖር  ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት የክትትልና ቁጥጥር ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አስታውቀዋል።

በሌላ በኩል የክልሉ ህብረት ሥራ ኮሚሽን የግብይት ትስስር ባለሙያ አቶ ፈንታሁን ወርቅዬ፤ የግብርናና የፍጆታ ምርቶች በዩኒየኖች፣ በሸማቾች ህብረት ሥራ ማህበራት እና በሁለተኛ ደረጃ የገበያ ማዕከላት በኩል እየቀረቡ መሆኑን ተናግረዋል።

ለበዓሉ ከ16 ሺህ ኩንታል በላይ ሽንኩርትና ጤፍ፣ 4 ሺህ 500 ኩንታል የዳቦ ዱቄት፣ ከአንድ ሚሊዮን ሊትር በላይ የምግብ ዘይት፣ እንቁላልና የወተት ተዋጽኦዎች  ማቅረብ መቻሉን ገልጸዋል።


 

በሁሉም ዘርፍ በቂ የምርት አቅርቦት በመኖሩ በተረጋጋ ሁኔታ የበዓል ገበያ ግብይት እየፈጸሙ መሆናቸውን የተናገሩት ደግሞ የባህር ዳር ከተማ ነዋሪዋ ወይዘሮ ስለናት ይዘንጋው ናቸው።

የዋጋ ንረትን ለመቋቋም መንግስት በየአካባቢው የጀመረውን የ2ኛ ደረጃ የገበያ ማዕከላትን የማስፋፋት ስራ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም