ቀጥታ፡

በክልሉ ለዘመን መለወጫ በዓል የምርት አቅርቦት እጥረት እንዳይከሰት በቂ ዝግጅት ተደርጓል

ወላይታ ሶዶ፤ ጳጉሜን 4/2018 (ኢዜአ) ፦በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ለዘመን መለወጫ በዓል የምርት አቅርቦት እጥረት እንዳይከሰት በቂ ዝግጅት መደረጉን የክልሉ ንግድና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ አስታወቀ።

የአዲስ ዘመን መለወጫ የበዓል ገበያን አስመልክቶ ኢዜአ ያነጋገራቸው የቢሮው ኃላፊ ወይዘሮ ሰናይት ሰለሞን እንደገለጹት፤ ለበዓሉ የሚያስፈልጉ ምርቶች በበቂ ሁኔታ እንዲቀርቡ ተደርጓል። 

ከዘመን መለወጫ በዓል በተጨማሪ በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች የሚከበሩ ህዝባዊ በዓላት እንዳሉ አስታውሰው፣ ለበዓል ገበያ በምርት አቅርቦቱ የተደረገው ዝግጅት ይህንንም ታሳቢ ያደረገ ነው ብለዋል።

ከምርት አቅርቦት በተጨማሪ በገበያው ተገቢ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ እንዳይኖር ሕብረተሰቡንና የተለያዩ አካላትን ያሳተፈ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ በልዩ ትኩረትና በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።


 

ወይዘሮ ሰናይት እንዳሉት መደበኛ ገበያዎችን ጨምሮ በክልሉ ባሉ ከ105 በላይ የቅዳሜና እሁድ ገበያዎች ምርቶች ለሸማቹ በቀጥታ የቀረቡ ሲሆን፣ የግብርና ምርቶችም የህብረተሰቡን አቅም ታሳቢ በማድረግ እንዲቀርቡ ተደርጓል፡፡

ከኢንተርፕራይዞች፣ ከክልሉ ዶሮ እርባታ ተቋምና ሌሎች አካላት ጋር በመነጋገር የዶሮና እንቁላል ምርት እንዲቀርብ መደረጉን የገለጹት ወይዘሮ ሰናይት፣ በበዓል ገበያ ከወትሮ የተሻለ አቅርቦት መኖሩንና የተረጋጋ ግብይት እየተካሔደ ይገኛል ብለዋል።

እንደ ኃላፊዋ ገለጻ፣ በክልሉ የሚገኙ የሸማች ሕብረት ሥራ ማህበራት ዘይት፣ ስኳር፣ ዱቄትና መሰል የኢንዱስትሪ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያቀርቡ ተደርጓል።


 

በበዓል ገበያ ለጤና ጠንቅ የሆኑ ባዕድ ነገሮች የተቀላቀበት ምርትን ማቅረብ ጨምሮ ሀሰተኛ የገንዘብ ኖቶች ሊዘዋወሩ ስለሚችል ህብረተሰቡ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርግና አጠራጣሪ ነገር ሲገጥመውም ፈጥኖ ጥቆማ በመስጠት እንዲተባበር አስገንዝበዋል።

የክልሉ ሕብረት ሥራ ልማት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳሙኤል ፎላ በበኩላቸው፤ ለዘመን መለወጫ በዓል አስፈላጊ የግብርና እና የፋብሪካ ምርቶች በስፋት መቅረባቸውን ተናግረዋል።


 

በክልሉ ያሉ 78 ሸማች መሰረታዊ ሕብረት ሥራ ማህበራት እና 3 ዩኒየኖች ከ25 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጭ የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶች ግዢ ፈጽመው ለገበያ ማቅረባቸውን ተናግረዋል።

በወላይታ ሶዶ ከተማ ነጋዴ የሆኑት አቶ አክሊሉ ጎዳና እንዳሉት፣ ከተለያዩ አካባቢዎች የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶችን በማስመጣት በተመጣጣኝ ዋጋ ለሸማቹ እያቀረቡ ይገኛሉ።


 

ወይዘሮ ፀሐይነሽ ካይሳሞ በበኩላቸው፤ በበዓል ገበያው የተሻለ የምርት አቅርቦት መኖሩ የሚፈልጉትን ምርት በአቅማቸው ለመሸመት እንዳስቻላቸው ተናግረዋል።


 

ምርቶችን በስፋት ከማቅረብ ባለፈ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ እንዳይኖር በቅንጅት እየተደረገ ያለው ቁጥጥርና ክትትል ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም