ሀገራዊ አንድነትን የሚያጠናክር አስተሳሳሪ የወል ትርክት ግንባታ ውጤት እያስመዘገበ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ሀገራዊ አንድነትን የሚያጠናክር አስተሳሳሪ የወል ትርክት ግንባታ ውጤት እያስመዘገበ ነው
አዲስ አበባ ፤ ጳጉሜን 4/2018 (ኢዜአ) ፦የኢትዮጵያን ዘርፈ ብዙ ብዝሃነትና ህብረ ብሔራዊነት መሠረት ያደረገ፣ ሀገራዊ አንድነትን የሚያጠናክር አስተሳሳሪ የወል ትርክት የመገንባት ተግባር ውጤት እያስመዘገበ መሆኑን የሕገ መንግሥትና ፌዴራሊዝም አስተምህሮ ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ኃይለኢየሱስ ታዬ (ዶ/ር) ገለጹ።
ህብረ ብሔራዊነትን ማጎልበት ሀገራዊ አንድነትን፣ ሰላምንና የልማት ዕድገትን ለማጠናከር ወሳኝ መሆኑንም ነው ዋና ዳይሬክተሩ የተናገሩት።
ኢትዮጵያ በህብረ ብሔራዊነት የደመቀች ለሀገራዊ እሴቶች እና ግቦች የሚተጉ እንዲሁም በጋራ እጣ ፈንታ የተሳሰሩ ህዝቦች ያሏት ሀገር ናት።
ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት ኃይለኢየሱስ ታዬ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ የኢትዮጵያን ብዝሃነት እና ህብረ ብሔራዊነት ለወል ትርክት ግንባታ በማዋል አስተሳሳሪ ትርክት ከመገንባት አኳያ ውጤቶች ተመዝግበዋል።
ኢትዮጵያ ህብረ ብሔራዊ ብዝሃነት ያላት ሀገር መሆኗን ጠቁመው፤ ይህንን ብዝሃነት በተገቢው መንገድ ማስተናገድ የጋራ ሀገራዊ ማንነትን ለመገንባት መሠረት መሆኑንም አክለዋል።
በዚህም ባለፉት ዓመታት የኢትዮጵያ ህብረ ብሔራዊነት በተገቢው በመመራቱ ለሀገር ጥንካሬ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
ህብረ ብሔራዊነት አንዱ የሀገራዊ ትርክት ግንባታ ማዕከል መሆኑን ገልጸው፤ ሁሉም ቋንቋዎች፣ ባህሎችና ማንነቶች ለሀገር ግንባታ ወሳኝ መሆናቸውን ተናግረዋል።
አሰባሳቢ ትርክት በሀገራዊ ስኬቶች፣ በልማትና በሀገሪቷ ህብረ ብሔራዊነት ላይ ሊመሠረት እንደሚችልም ነው ጨምረው የገለጹት።
የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን አከባበር የኢትዮጵያ ህብረ ብሔራዊነት ጎልቶ የሚታይበት ብቻ ሳይሆን ሀገራዊ አንድነት የሚጠናከርበት መሆኑን ጠቁመዋል።
ማዕከሉ የኢትዮጵያ ህብረ ብሔራዊነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ግንዛቤ በመፍጠር በኩል በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝም አስታውቀዋል።
የፌዴራል ሥርዓቱ የሚጠይቀው ዕውቀት፣ ክህሎትና አስተሳሰብ እንዲጎለብትም በርካታ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ጨምረው ገልጸዋል።
ፌዴራሊዝም በብዝሃነት የተገነባች ሀገር ውስጥ የተለያዩ ማንነቶችን አሳታፊ በሆነ መንገድ ለማስተናገድና የጋራ ሀገር ግንባታን ለማጠናከር ጠቃሚ ሥርዓት መሆኑንም ተናግረዋል።
አክለውም የፌዴራሊዝም ሥርዓቱ የተለያዩ አካባቢዎች ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩና አካባቢያቸውን እንዲያለሙ ዕድል በመስጠት የልማት አቅሞችንና ፍላጎቶችን ለማስታረቅ አግዟል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ህዝብ በብዝሃነት ውስጥ አብሮ የመኖር ልምድ ማካበቱንና ይህንን የአብሮነት እሴት ወደ ሀገራዊ የጋራ እሴትነት ለማሸጋገር በተከናወኑ ተግባራት በርካታ ውጤቶች መመዝገባቸውን ጠቁመው፤ ይህም ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።
ስለሆነም ህብረ ብሔራዊነትን ከፌዴራሊዝም እና ከዴሞክራሲ እንዲሁም ከልማትና ከሀገራዊ እሴቶች ጋር በማጣመር የጋራ ሀገራዊ ማንነትና አንድነትን ለማጠናከር በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸዋል።