ቀጥታ፡

በመዲናዋ ለዘመን መለወጫ በዓል በቂ የግብርና ምርቶች ቀርበዋል

አዲስ አበባ ፤ ጳጉሜን 4/2018 (ኢዜአ) ፦ለዘመን መለወጫ በዓል በቂ የግብርና ምርቶች አቅርቦት መዘጋጀቱን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአርሶ አደርና ከተማ ግብርና ኮሚሽን አስታወቀ፡፡ 

ለመጪው የ2019 አዲስ ዓመት በዓል የሚቀርቡ የግብርና ምርቶች ጥራት እና ደህንነት ላይ የቁጥጥር ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑንም ኮሚሽኑ አስታውቋል፡፡

የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር ፀጋ ለማ (ዶ/ር) በሰጡት መግለጫ፤ ከነሐሴ 28 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ የገበያ ባዛሮችና ማዕከላት ስጋ፣ ዶሮ እና እንቁላል በተመጣጣኝ ዋጋ እየቀረበ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ከምርት ጥራትና ደህንነት አንጻር በከተማዋ በሚገኙ ሶስት የቄራ ድርጅቶች ውስጥ ከ40 በላይ ስጋ መርማሪ ሀኪሞች ተመድበው ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።

በተጨማሪም የስጋ ደህንነትን ለማረጋገጥ ለስጋ ማጓጓዣ ተሽከርካሪዎች ልዩ የጥራት ደረጃ ተዘጋጅቶ ስርጭቱ እየተከናወነ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል፣ የወተት ምርት ጥራትና ደህንነትን ከመጠበቅ እስከ ስርጭት ባሉ ሂደቶች ተገቢውን ቁጥጥር ማድረግ የሚያስችል የአቅም ግንባታ ስራዎች መሰራታቸውን እና የጥራት መፈተሻ መሳሪያዎች እየተሟሉ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

ሕብረተሰቡ በበዓል ወቅት በሚያከናውነው ግብይትና የቅርጫ እርድ ወቅት ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርግም ምክትል ኮሚሽነሩ አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም