የኢትዮጵያውያን ኅብር በውጤት የተገለጠበት - አረንጓዴ አሻራ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያውያን ኅብር በውጤት የተገለጠበት - አረንጓዴ አሻራ
(በሙሴ መለሰ)
ኢትዮጵያ ባለፉት አሥርት ዓመታት የደን መመናመን፣ የአፈር መሸርሸር፣ የለም መሬት እየቀነሰ መምጣት እና ተደጋጋሚ ድርቅን ጨምሮ እጅግ አስቸጋሪና ተደራራቢ የአየር ንብረት ለውጥ ፈተናዎች ይገጥሟት ነበር።
ይህ የስነ-ምህዳር መዛባት በሚሊዮን የሚቆጠሩ አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮችን ህይወትና የምግብ ዋስትና አደጋ ላይ ጥሎት ቆይቷል።
በተለይም በቆላማ እና ከፊል አርብቶ አደር በሆኑት የሀገሪቱ አካባቢዎች የውሃ ምንጮች መድረቅ እና የግጦሽ መሬቶች መውደም ሰብአዊ ህይወቶችንና የቁም እንስሳትን ለአደጋ አጋልጧል።
የብዝሃ ህይወት መመናመን ሌላኛው ፈተና ተደርጎ የሚወሰድ ሲሆን፣ ይህ የተፈጥሮ ሀብት መመናመን በሀገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገትና ልማት ጎዳና ላይ ትልቅ ተግዳሮት ሆኖ ቆይቷል።
ኢትዮጵያ ይሄን የአየር ንብረት ለውጥ በዘላቂነት ለመከላከል እና የተፈጥሮ ሀብትን ለመጠበቅ ከቃል ያለፈ የተግባር ስራ ከጀመረች ዓመታት ተቆጥረዋል።
የዚህ ሀገራዊ ስራ አበይት መገለጫ ከሆኑ ብሔራዊ ኢኒሼቲቮች መካከል “አረንጓዴ አሻራ” ተጠቃሽና ግንባር ቀደም መርሃ ግብር ነው።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት በ2011 ዓ.ም የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር፣ የደን መመናመንን ለመግታትና ሥነ-ምህዳርን ለመመለስ የተጀመረ ታላቅ ሀገራዊ ንቅናቄ ነው።
ይህ ስራ ዛፍ የመትከል ዘመቻ ብቻ ሳይሆን፣ ኢትዮጵያውያን በአንድነትና በህብር በመቆም በጋራ የሰሩበት ታላቅ ህብረተሰባዊ አቅም የታየበት ማረጋገጫም ሆኗል።
ሀገሪቱ እ.አ.አ በ2027 የሚካሄደውን ታላቁን የዓለም አቀፍ አየር ንብረት ጉባኤ (ኮፕ 32) በዋና ከተማዋ አዲስ አበባ እንድታስተናግድ መመረጧ፣ በአረንጓዴ ልማት ያሳየችው የህብርና የአንድነት ጉዞ ያስገኘው ትልቅ ዓለም አቀፋዊ ድል ነው።
በአረንጓዴ አሻራ ስኬት ትልቁ መገለጫ የህዝቦች የጋራ ትብብር እና ተደጋግፎ መስራት መሆኑን በተግባር ለማሳየት ተችሏል።
የኢትዮጵያ የደን ሽፋን በ2010 ዓ.ም ከነበረበት 17.2 በመቶ በጥቂት ዓመታት ውስጥ ማለትም በ2017 ዓ.ም ወደ 23.6 በመቶ ማደግ ችሏል።
እስካሁን ከ54 ቢሊዮን በላይ ችግኞች የተተከሉ ሲሆን፣ በየዓመቱ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች በአንድነት በመሳተፍ ለአየር ንብረት ተጋላጭ የነበሩ አካባቢዎች አረንጓዴ ለብሰው እንዲለወጡ አድርገዋል።
በብራዚል ቤለም በተካሄደው 30ኛው የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ጉባኤ ላይ የአፍሪካ ተደራዳሪዎች ቡድን ኢትዮጵያን የኮፕ 32 አስተናጋጅ አድርጎ በሙሉ ድምፅ መምረጡ የህብር እና የአንድነት ውጤት ነው።
የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ስኬት የተለካው ችግኝ በመትከል ብቻ ሳይሆን፣ ህዝብና መንግስት በህብር ተክሎ የማሳደግና የመንከባከብ ባህልን በማዳበር ሲሆን የተተከሉ ችግኞች የመጽደቅ ምጣኔ ከ85 በመቶ በላይ ሆኗል።
ይህ ሂደት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ከአቮካዶ፣ ማንጎና ፓፓያ የመሳሰሉ የፍራፍሬ ችግኞች መተከል ጋር ተያይዞ የግብርና ምርታማነትን ያሳደገ ሲሆን፣ ለብዙ ዜጎች የሥራ ዕድል ፈጥሯል።
መርሃ-ግብሩ ከደን ዛፍ ችግኝ ባለፈ የምግብ እና የከተማ ውበት መሰረት የሆኑትንም ያካተተ በመሆኑ ውጤቱን የላቀ አደርጎታል። የግብርና ምርታማነት እንዲጨምርም ጉልህ አስተዋጽኦ እያደረገ ይገኛል።
አረንጓዴ አሻራ የአየር ንብረት ለውጥን ለመዋጋት የተደረገ የአካባቢ ጥበቃ ስራ ብቻ ሳይሆን፣ ሕዝቦች በአንድነትና በህብር ሲሰለፉ ሀገራቸውንና መልክዓ ምድራቸውን መቀየር እንደሚችሉ ለዓለም ያሳዩበት ታላቅ ማረጋገጫ ነው።