አዲሱ ዓመት ተጨማሪ ዲፕሎማሲያዊ ድሎችን ለማስመዝገብ የበለጠ የምንሰራበት ነው - ኢዜአ አማርኛ
አዲሱ ዓመት ተጨማሪ ዲፕሎማሲያዊ ድሎችን ለማስመዝገብ የበለጠ የምንሰራበት ነው
አዲስ አበባ ፤ ጳጉሜን 4/2018 (ኢዜአ) ፦አዲሱ ዓመት ባለፈው ዓመት ከተመዘገቡት ዲፕሎማሲያዊ ስኬቶች በመነሳት ተጨማሪ ድሎችን ለማስመዝገብ፣ አዲስ ዕይታን ለመላበስና አዲስ ክህሎትን ለማዳበር ትልቅ አጋጣሚ የሚፈጥር መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አዳም ተስፋዬ ገለጹ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ተጠሪ ተቋማት ጳጉሜን 4 የኅብር ቀንን ‘’ብዝኃነት የኢትዮጵያ ጌጥ" በሚል መሪ ሐሳብ በጋራ አክብረዋል፡፡
በበዓሉ ሥነ-ሥርዓት ላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና የተጠሪ ተቋማት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ ዲፕሎማቶች እንዲሁም የጽሕፈት ቤቱ ሠራተኞች ተገኝተዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አዳም ተስፋዬ በዚሁ ወቅት ባስተላለፉት መልእክት፤ በተጠናቀቀው ዓመት በመሠረተ ልማት፣ በኢኮኖሚ፣ በአካባቢ ጥበቃና በዲፕሎማሲ ዘርፎችና በሌሎችም ከፍተኛ ስኬቶች መመዝገባቸውን ገልጸዋል።
የጳጉሜን ቀናት እመርታን፣ ማንሠራራትን፣ ጽናትን፣ ኅብርንና ነገን በማሰብ ስኬቶችን የምንቆጥርበት እንዲሁም ለአዲሱ ዓመት አዲስ ራዕይ የምንሰንቅበት ወቅት ነው ሲሉም አብራርተዋል።
የተመዘገቡትን የዲፕሎማሲ ስኬቶች መሠረት በማድረግ በአዲሱ ዓመት ለላቀ ውጤት እና ለተጨማሪ ድሎች በቁርጠኝነት እንደሚሰራ አስገንዝበዋል።