በወልቂጤ ከተማ ለበዓል ገበያ የኢንዱስትሪና ግብርና ምርቶች እንዲሁም የእርድ እንስሳት በተለያዩ አማራጮች ቀርበዋል - ኢዜአ አማርኛ
በወልቂጤ ከተማ ለበዓል ገበያ የኢንዱስትሪና ግብርና ምርቶች እንዲሁም የእርድ እንስሳት በተለያዩ አማራጮች ቀርበዋል
ወልቂጤ ፤ ጳጉሜን 4/2018 (ኢዜአ) ፦ ለአዲስ ዓመት የበዓል ገበያ የኢንዱስትሪና ግብርና ምርቶች እንዲሁም የእርድ እንስሳት በተለያዩ አማራጮች መቅረባቸውን በማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የወልቂጤ ከተማ ንግድና ገበያ ልማት ፅ/ቤት አስታወቀ።
በጳጉሜን ወር እለቶቹን በተለያዩ መርሃ ግብሮች ከማክበር በተጓዳኝ ኢትዮጵያዊያን አዲስ ዓመትን ለመቀበል በዝግጅት ላይ ይገኛሉ።
በዚሁ መሰረትም የግብርና እና ኢንዱስትሪ ምርቶች፣ የእርድ እንስሳት፣ አልባሳትና ሌሎችንም በመሸመት አዲሱን ዓመት ለመቀበል እየተዘጋጁ ነው።
በማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ወልቂጤ ከተማና አካባቢው የበዓል ግብይትና አቅርቦቱን በተመለከተ የኢዜአ ሪፖርተር ቅኝት በማድረግ የሚመለከታቸውን የስራ ሃላፊዎችና ሸማቾችን አነጋግሯል።
የወልቂጤ ከተማ ንግድና ገበያ ልማት ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ ግርማ ንቅበሸዋ፤ ለበዓል የምርቶችና የእርድ እንስሳት አቅርቦት በበቂ ሆኔታ መኖሩን ገልጸዋል።
ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እንዲሁም ከንግዱ ማህበረሰብ ጋር ቀደም ብሎ በቅርበት በመነጋገር ለበዓል ገበያ ዝግጅት መደረጉን አንስተው በዚህም በተመጣጣኝ ዋጋ በቂ አቅርቦት እንዲኖር ማድረግ ተችሏል ብለዋል።
የቅዳሜ እና እሁድ ገበያን ጨምሮ በተለያዩ የገበያ አማራጮች በብዛትና በተለያዩ አማራጮች መቅረቡን አንስተው ህገ ወጥ ግብይትና ያልተጋባ ዋጋ ጭማሬ እንዳይኖር ጥብቅ ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል።
በኢትዮጵያ ንግድ ስራዎች ኮርፖሬሽን የወልቂጤ ቅርንጫፍ ተጠሪ ናትናኤል ደበበ፤ ከእርሻ አርሶ አደሮች በቀጥታ በሚያመጡት ምርት፤ ከፋብሪካ እና ከቅዳሜ እና እሁድ ገበያ ምርቶች በብዛትና በጥራት ለሸማቾች መቅረቡን ተናግረዋል።
ለበዓል ሲሸምቱ ካገኘናቸው መካከል አቶ ጥበበ ታምሩ፣ ወይዘሮ አመለወርቅ ታደሰ እና ወይዘሮ ብርዝነሽ አረጋ፤ የበዓል ገበያ አቅርቦቱ ብዙ አማራጮች ያሉት በመሆኑ በተመጣጣኝ ዋጋ በመግዛት ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።