በካራባኦ ካፕ ቼልሲ ከሊድስ ዩናይትድ ጋር ይጫወታል - ኢዜአ አማርኛ
በካራባኦ ካፕ ቼልሲ ከሊድስ ዩናይትድ ጋር ይጫወታል
አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 4/2018 (ኢዜአ):- በእንግሊዝ ካራባኦ ካፕ የሶስተኛ ዙር መርሐ ግብር ቼልሲ ከሊድስ ዩናይትድ ጋር ዛሬ ጨዋታውን ያደርጋል።
ጨዋታው ምሽት አራት ሰዓት ላይ በስታምፎርድ ብሪጅ ስታዲየም ይካሄዳል።
በሁለተኛ ዙር ቼልሲ ሉተን ታውንን፣ ሊድስ ዩናይትድ ኖቲንግሃም ፎረስትን በተመሳሳይ 2 ለ 0 አሸንፈዋል።
ክለቦቹ በውድድሩ ታሪክ ሁለቱ ጊዜ ተገናኝተው ቼልሲ በሁለቱም ጨዋታዎች አሸንፏል።
እ.አ.አ በ2001 በአራተኛ ዙር ተገናኝተው ቼልሲ 2 ለ 0 አሸንፏል። ቡድኖቹ እ.አ.አ በ2012 በሩብ ፍጻሜው ባደረጉት ጨዋታም ቼልሲ 5 ለ 1 ተጋጣሚውን ረትቷል።
ከ14 ዓመታት በኋላ ዳግም በካራባኦ ዋንጫ ተገናኝተዋል።
ቼልሲ የካራባኦ ዋንጫን አምስት ጊዜ ያነሳ ሲሆን ለመጨረሻ ጊዜ አሸናፊ የነበረው እ.አ.አ በ2015 ነው።
ሊድስ ዩናይትድ እ.አ.አ በ1968 ውድድሩን ማሸነፍ ችሏል።
ባለሜዳው ቼልሲ ጨዋታውን የማሸነፍ የቅድሚያ ግምት አግኝቷል።
የ39 ዓመቱ አውስትራሊያዊ ጃሬድ ጊሌት ጨዋታውን በዋና ዳኝነት ይመሩታል።