ግብጽ ጊዜው ያለፈበትን አካሄድ በመተው በአባይ ወንዝ ላይ ያለውን አዲስ እውነታ መቀበል አለባት-ቲቦር ናጊ - ኢዜአ አማርኛ
ግብጽ ጊዜው ያለፈበትን አካሄድ በመተው በአባይ ወንዝ ላይ ያለውን አዲስ እውነታ መቀበል አለባት-ቲቦር ናጊ
አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 4/2018 (ኢዜአ)፦ግብጽ ጊዜው ያለፈበትንና ዘመኑን የማይመጥን አካሄድ ትታ በአባይ ወንዝ ላይ ያለውን አዲስ እውነታ መቀበል አለባት ሲሉ የቀድሞው የአሜሪካ የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቲቦር ናጊ ገለጹ።
የቀድሞው የአሜሪካ ዲፕሎማት አባይን በተመለከቱ ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ ከፐልስ ኦፍ አፍሪካ ጋር ቆይታ ማድረጋቸውን በኤክስ ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ገልጸዋል።
ግብፅ አሁን ያለንበት ዘመን 19ኛው እና 20ኛው ክፍለ ዘመን ሳይሆን 2026 መሆኑን በውል ከተገነዘበች ከኢትዮጵያ ጋር አባይን በተመለከተ ሁለቱንም ወገኖች አሸናፊ የሚያደርግ ስምምነት ላይ መድረስ እንደሚቻል አፅንኦት ሰጥተው መናገራቸውን አመልክተዋል።
ቲቦር ናጊ ከፐልስ ኦፍ አፍሪካ ጋር በቅርቡ በነበራቸው ቆይታ የኢትዮጵያን በውሃ ሃብቷ የመልማት መብት ግብጽ ልታከብር እንደሚገባ ገልጸዋል።
የቀጣናው ፖለቲካዊ ገጽታ ከፍተኛ ለውጥ ማሳየቱን የገለጹት ቲቦር ናጊ፣ ግብፅ በአሁኑ ሰዓት አዲስ የኃይል ሚዛን መፈጠሩንና ኢትዮጵያም እጅጉን ማደጓን ልትገነዘብ እንደሚገባ አስምረውበታል።
ግብፅ የድርድር አቀራረቧን ዳግም በመመርመርና አዲስ እና አዎንታዊ አመለካከት ይዛ ወደ ንግግር ጠረጴዛው ከተመለሰች ዘላቂና ፍትሃዊ ስምምነት ላይ መድረስ እንደሚቻልም ነው ያነሱት።
የሁሉንም የተፋሰሱ ሀገራት የውሃ ሀብቶችን የመጠቀም መብት እውቅና መስጠት ላይ የተመሰረቱ ውይይቶች የጋራ መግባባት ሊፈጥሩ እንደሚችሉም ተናግረዋል።
ቲቦር ናጊ የኢትዮጵያ የራሷን የተፈጥሮ ሃብት መጠቀም ራስ ወዳድነት ወይም በግብፅ ላይ የህልውና አደጋ ተደርጎ መታየት የለበትም ሲሉ አስገንዝበዋል።
አገራት የራሳቸውን የተፈጥሮ ሃብት ይጠቀማሉ። ሁሉንም ነገር በእውነታው ላይ ቆመን እንመልከት ብለዋል።
የቀድሞ የአሜሪካ የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቲቦር ናጊ ኢትዮጵያ የባህር በር ለማግኘት የምታደርገውን ጥረት በተመለከተም ሀሳባቸውን አንስተዋል።
የኢትዮጵያ የባህር በር የማግኘት ፍላጎት ፍትሃዊና ሕጋዊ ጥያቄ መሆኑን የገለጹት ቲቦር ናጊ፣ የጎረቤት ሀገራት የኢትዮጵያን ፍላጎቶች በሚገባ መረዳት እንደሚገባቸው አሳስበዋል።