ህብረ ብሔራዊ አንድነትን በማጠናከር ኢትዮጵያን አጽንቶ ማቆየት ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
ህብረ ብሔራዊ አንድነትን በማጠናከር ኢትዮጵያን አጽንቶ ማቆየት ይገባል
አርባ ምንጭ ፤ ጳጉሜን 4/2018 (ኢዜአ) ፦ህብረ ብሔራዊ አንድነትን በማጠናከር ኢትዮጵያን አጽንቶ ማቆየት ይገባል ሲሉ የጋሞ የሀገር ሽማግሌዎች ገለጹ።
ኢትዮጵያ በበርካታ ቋንቋዎች፣ ባህሎች፣ እሴቶችና ታሪኮች የተሸለመች ሕብረ-ቀለማዊ ሀገር ናት። ይህም አንዱ የሌላውን ባህልና መብት አክብሮ፣ በአንድነትና በእኩልነት ላይ የተመሠረተ ጠንካራ ማህበረሰብ ለመገንባት መሠረት ሆኗል።
ሕብር ማለት መለያየት ሳይሆን በልዩነት ውስጥ ያለ ውበት፣ በጥንካሬ የተሳሰረ ወንድማማችነትና እህትማማችነት ነው።
በኢትዮጵያ በየዓመቱ የጳጉሜን ቀናት አብሮነትን፣ ጽናትን፣ የሀገር እድገትንና ስኬትን በሚያጎሉ ልዩ ልዩ ሁነቶች ተሰይመው ይከበራሉ።
ከእነዚህም መካከል «የሕብር ቀን» የኢትዮጵያ መገለጫ የሆነውን ብዝሃነት በማጠናከር ለሀገር ልማትና እድገት ጉዞ የጥንካሬ ምንጭ መሆኑን በሚያጎለብት መልኩ ዛሬ ጳጉሜን 4 ቀን እየተከበረ ይገኛል።
የሕብር ቀንን በማስመልከት ኢዜአ ያነጋገራቸው የጋሞ ሀገር ሽማግሌዎች ኢትዮጵያን አጽንቶ ለማቆየት ሕብረ-ብሔራዊ አንድነትን በማጠናከር ለጋራ ስኬት መትጋት እንደሚገባ ገልጸዋል።
አስተያየታቸውን ከሰጡት መካከል የጋሞ ሀገር ሽማግሌ ኤልዶ ኤማኔ፤ ኢትዮጵያ የበርካታ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መኖሪያ መሆኗን አንስተው ህዝቦች በእኩልነት፣ በአብሮነት፣ በመከባበርና በመቻቻል ለዘመናት መኖራቸውን ተናግረዋል።
ብዝሃነት የኢትዮጵያውያን ውበት በመሆኑ ኢትዮጵያ አሁን የደረሰችበትን የእድገት ጉዞ ለማስቀጠል በሕብረት መቆም አማራጭ የሌለው ተግባር መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በመሆኑም የተመዘገቡ የልማት ስኬቶችን፣ድሎችን ፣አብሮነትና አንድነትን አስጠብቆ ማስቀጠል እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ዘመን የተሻገሩ ችግሮችን በመመካከር ለመፍታት አካታች ሆኖ የተካሄደው ሀገራዊ ምክክር ትልቅ ስኬት መሆኑንም ጠቅሰዋል።
በደስታም ሆነ በሀዘን ጊዜ በአንድነት የሚቆም ጠንካራ የጋራ እሴት እንዳለ የተናገሩት ደግሞ ሌላው የጋሞ ሀገር ሽማግሌ አዳሙ ኪሮ ናቸው።
በዋናነትም የሠርግ፣ የለቅሶ፣ የደቦ እና ሌሎች በርካታ ሕብረ-ብሔራዊነትን የሚገልጹ የጋራ እሴቶች በስፋት እንዳሉ ነው ያመለከቱት።
ዛሬ የሚታሰበው የሕብር ቀን የሀገራችንን ባህሎችና እሴቶች ለማጎልበት እንዲሁም አንድነትና አብሮነትን ለማጠናከር ትልቅ ፋይዳ እንዳለውም ጠቅሰዋል።
ሕብረ-ብሔራዊነትና ኢትዮጵያዊነት የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች መሆናቸውን የገለጹት ሀገር ሽማግሌው፤ የጋራ ትርክቶችን በመገንባት ሀገርንና ሰላምን ማጽናት እንደሚገባ አሳስበዋል።
ሀገራችን ጸንታ እንድትቆይ ወጣቱን ትውልድ ስለ አንድነት፣ ባህልና እሴቶች ማስተማር ከአባቶች የሚጠበቅ ኃላፊነት መሆኑንም አመላክተዋል።