ቀጥታ፡

በአዳማ ከተማ ለዘመን መለወጫ በዓል መሰረታዊ የፍጆታ እቃዎች በተመጣጣኝ ዋጋ ቀርበዋል

አዳማ ፤ ጳጉሜን 4/2018 (ኢዜአ) ፦ለዘመን መለወጫ በዓል የሚሆኑ መሰረታዊ የፍጆታ እቃዎች በተመጣጣኝ ዋጋና በበቂ ሁኔታ ለገበያ መቅረባቸውን በአዳማ ከተማ የሚገኙ ሸማቾችና ነጋዴዎች ገለጹ።

በአዳማ ከተማ ለዘመን መለወጫ በዓል በተከፈተው ባዛር መሰረታዊ የፍጆታ እቃዎች በበቂ መጠን ለሸማቹ ህብረተሰብ ተደራሽ መሆናቸውን ያነጋገርናቸው አምራቾችና ሸማቾች ገልጸዋል።


 

የዲና ዱቄት ፋብሪካ የሽያጭ ተወካይ አቶ ጅማ ተንኮሉ እንደገለጹት፤ ፋብሪካቸው በከተማ አስተዳደሩ በተዘጋጀው ባዛር ላይ በመሳተፍ ለአዲስ ዓመት በዓል የሚሆኑ የምግብ እህሎችን በጥራትና በተመጣጣኝ ዋጋ ለህብረተሰቡ እያቀረበ ይገኛል።


 

በፋብሪካው ለገበያ ከቀረቡት ምርቶች መካከል ቀይና ነጭ ጤፍ፣ የፍርኖ ዱቄት እንዲሁም የበቆሎ ዱቄት ተጠቃሾች ሲሆኑ፤ ምርቶቹ እንደ ሸማቹ ፍላጎትና አቅም በ5፣ በ10፣ በ25 እና በ50 ኪሎ ግራም  መቅረባቸውን ገልጸዋል።

የበዓል የፍጆታ ምርቶች በበቂ መጠንና በተመጣጣኝ ዋጋ መቅረቡ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል እንደ አቅሙ ሸምቶ በዓሉን በደስታ እንዲያከብር የጎላ አስተዋጽኦ እንዳለው አብራርተዋል።

የጎልደን ፉል ዘይት ፋብሪካ የሽያጭ ሰራተኛ ቃልኪዳን ሽፈራው በበኩላቸው፤ ፋብሪካው መጪውን የ2019 አዲስ ዓመት አስመልክቶ የገበያ መረጋጋትን ለመፍጠር ሰፊ ዝግጅት ማድረጉን ገልጸዋል። 


 

በዚህም መሰረት ከሁለት እስከ አምስት ሊትር መጠን ያለው የምግብ ዘይት በተመጣጣኝ ዋጋና በበቂ ሁኔታ በባዛሩ ማቅረቡን ተናግረዋል።

ሸማቹ ህብረተሰብ በከተማዋ ወደተከፈቱ የበዓል ባዛሮች በመሄድ የሚፈልጋቸውን የፍጆታ ምርቶች በተመጣጣኝ ዋጋ መሸመት እንደሚችልም ገልጸዋል።

ለበዓል ሲሸምቱ ካገኘናቸው ሸማቾች መካከል ወይዘሮ ዓለም ንጉሴ በበኩላቸው፤ ለበዓሉ የሚያስፈልጉ መሰረታዊ የፍጆታ እቃዎች በባዛሩ በበቂ ሁኔታ መቅረባቸውን ገልጸዋል።


 

አምራች ኢንዱስትሪዎችና ነጋዴዎች በባዛሩ ላይ እያቀረቡት ያለው የፍጆታ ምርት የገበያ ዋጋን በማረጋጋት በኩል ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ወይዘሮ ዓለም ገልጸዋል። 

ለበዓል ፍጆታ የሚሆን የምግብ ዘይት፣ ሽንኩርትና ሌሎችንም ማጣፈጫዎች በተመጣጣኝ ዋጋ መሸመታቸውን ተናግረዋል።

ሌላኛው ሸማች አቶ አክሊሉ ዘውዴ፤ የከተማ አስተዳደሩ ዘመን መለወጫ በዓልን ምክንያት በማድረግ ባዛር በማዘጋጀትና ከአቅራቢዎች ጋር በመቀናጀት ያለምንም ደላላ ጣልቃ ገብነት ምርቶች በቀጥታ ለሸማቹ እንዲደርሱ ማድረጉ የበዓል ገበያው እንዲረጋጋ ማድረጉን ገልጸዋል።


 

ይህም በዓሉን ምክንያት በማድረግ በሚፈጠር አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪ በህብረተሰቡ ላይ የሚደርሰውን ጫና እየቀነሰው መሆኑን አቶ አክሊሉ ተናግረዋል።

የአዳማ ከተማ አስተዳደር ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ብዙነህ ግርማ እንደገለጹት፤ ኢንቨስትመንት ግሩፑ የዘመን መለወጫ በዓልን ምክንያት በማድረግ የተለያዩ የበዓል ፍጆታ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለህብረተሰቡ ለማቅረብ የግብይት ባዛር አዘጋጅቷል።


 

በባዛሩ ላይ ከ300 የሚበልጡ አምራች ኢንዱስትሪዎች፣ መሰረታዊ ህብረት ስራ ማህበራት፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች እንዲሁም ነጋዴዎች መሳተፋቸውንም አቶ ብዙነህ አስታውቀዋል።

አስተዳደሩም መጪውን የዘመን መለወጫ በዓል ምክንያት በማድረግ በገበያው ላይ የምርት አቅርቦት እጥረትና የዋጋ ንረት እንዳይከሰት እንዲሁም ህገ-ወጥ የንግድ እንቅስቃሴዎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ግብረ ሀይል አቋቁሞ እየሰራ መሆኑንም አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም