ሕብራዊነት- የኢትዮጵያ ልክና መልክ - ኢዜአ አማርኛ
ሕብራዊነት- የኢትዮጵያ ልክና መልክ
ምድረ ቀደምቷ ኢትዮጵያ ከዕውነተኛ የሰው ዘር ምንጭነቷ ባሻገር በአይነተ-ብዙ ሥነ ምህዳር የታደለች፣ ለኑሮ የሚስማማ ከባቢ የተቸራት ውብ ምድር ናት።
የመልክዓ ኢትዮጵያን ኅብራዊነት፤ ሀገሬው ብቻ ይሆን በየዘመናቱ ደጇን የረገጡ የባሕር ማዶ ጎብኚዎችም መስክረዋል።
ዕውቁ ኢጣሊያዊ የሥነ ሰብዕ ሊቅ ካርሎ ኮንቲ ሮሲኒን ኢትዮጵያ በብዝሀ ነገዶቿ፣ በባህልና ቋንቋ ባለቤትነቷ ‘የብዝሀ ማንነቶች ማህደር’ ናት ብለዋታል።
በኢትዮጵያ ሕዝብ ታሪክ፣ ባሕልና ማህበረሰብ አወቃቀር ጥናታቸው በስፋት የሚታወቁት አሜሪካዊው ፕሮፌሰር ዶናልድ ሌቪን ‘ትልቋ ኢትዮጵያ የባህል አውድማ‘ ይሏታል።
የትልቋ ኢትዮጵያ ሕዝቦች የተለያዩ ባህላት ፈጥረው፤ በልዩ ልዩ ጎሣ ተከፋፍለው፤ ለየብቻቸው ተፈናጥረው፣ ተገንጥለውና ተሸሽገው አልኖሩም። በትንሹ ባለፉት ሁለት ሺህ ዓመታት ውስጥ በንግድ፣ በጦርነት፣ በሃይማኖት ጉዳይ፣ በመዘዋወር፣ በጋብቻና ልዩ ልዩ አገልግሎቶችን በመለዋወጥ እርስ በርሳቸው ሲገናኙ ኖረዋል።
ታላቁ ደራሲና ዲፕሎማት ሀዲስ ዓለማየሁ ኢትዮጵያ ልዩ ልዩ ዘር፣ እምነት ባህልና ቋንቋ ያላቸው ነገዶች የሚኖሩባት ሀገር መሆኗን ይጠቅሳሉ። በየዘመናቱ የነበሩ ነገስታት ልዩ ልዩ ነገዶችን በማስተባበር የኢትዮጵያን ነጻነትና አንድነት ጠብቀው መዝለቃቸውን ያነሳሉ።
ኢትዮጵያውያን ስውር ስፍ ናቸው፤ መልካቸውም ሕብራዊ ነው።
ኢትዮጵያውያን ውስጣዊ የአለመግባባት እንከኖች ቢኖርባቸው እንኳን በሀገራቸው ክብር፣ ሉዓላዊነት እና ነጻነት ግን አልተደራደሩም።
ይልቁኑም ሀገር ስትወረር በኅብር ተመዋል፤ በጋራ መስዋዕትነት ውብ ሀገር አውርሰውናል።
ለኢትዮጵያ የተደረጉ ተጋድሎዎች፣ የኅብረ ብሔራዊ ሥልጣኔዎች እና የጋራ ታሪኮች ደግሞ ለአሰባሳቢ የወል ትርክት እርሾ ናቸው።
ሙዐዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ‘የትርክት ዕዳና በረከት’ በተሰኘው መፅሐፋቸው “ሕብረ ብሔራዊነት የኢትዮጵያ ጥንታዊ ታሪኳና መልኳ ነው” ይላሉ።
በተለይም በሰዎች የተንቀሳቃሽነት ተፈጥሯዊ ባህሪ፣ ንግድ፣ አስተዳድርና ሌሎች ምክንያቶችን በማውሳት “የሥልጣኔዎች መጀመር ዋናው ምክንያት የሰዎች ኅብረ ብሔራዊነት ነው” ሲሉም የቀደምት ሥልጣኔዎቻችን የኅብረ ብሔራዊነት እሴት እንዳላቸው ጠቅሰዋል።
ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም “ሕዝብነት በግዴታ ተገናኝቶ በውዴታ መሰተሳሰር ነው፤ ወይም በግዴታ ተገናኝቶ በውዴታ አብሮ መኖር ነው” ይላሉ።
ዶክተር ኃይሉ ወልደሚካኤል የተባሉ ምሁር ‘አብሮነት በኢትዮጰያ’ በተሰኘ መጽሐፋቸው ኢትዮጵውያን በተፈጥሮ ህግ አስገዳጅነት በየዘመናቱ ተወራርሰዋል ይላሉ።
የአንዱ ሕልውና በአንዱ ላይ የቀጠለ እንጂ ፍጹም ራሱን ሆኖ በሕልውና መከሰት አይቻልም። እናም አንዱ ማንነት በአንዱ ማንነት እየዳበረ የመጣ ነው ይላሉ።
ኢያሱ በካፋ የተባሉ ፀሐፊ “እኛ ኢትዮጵያውያን ብዙ የሚያመሳስሉን፣ ብዙ ያስተሳሰሩን፤ ብዙ ደምና አጥንት አብረን የከፈልንባቸው፣ ብዙ አጥንቶች ለሀገራችን የከስከስንባቸው ትልቅ አንፀባራቂ የጋራ ድሎች አሉን፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን ከማንም ያነስን አይደለንም” ሲሉ ይተነትናሉ።
ኢትዮጵያን ብዙ ጠላቶች በየዘመናቱ ተነስተውባታል። ግን ድል ነስታለች። ይህ ደግሞ ሕብራዊነት ወይንም የጋራ ተጋድሎ እና የመስዋዕትነት አሻራ ነው። ለዚህ ነው ሕብረ ብሔራዊ አንድነት ለነገዋ ኢትዮጵያ ሕልውና ዘላቂ ዋስትና የሚሰኘው!!
የሕብር ቀንን ስንዘክር ኢትዮጵያውን በመፈቃቀድና በፍቅር የመኖር እሴትን ልናስቀጥል፣ ለጋራ ሀገር ክብርና ከፍታ በኃላፊነትና በአንድነት ልንተጋ፣ ለልማትና ብልጽግናዋ ልንታትር ትልቅ የቤት ስራ ይዘን ነው።