ቀጥታ፡

የፀጥታና ደህንነት ተቋማት በመጠናከራቸው ኢትዮጵያን የማትበገርና የጸናች ሀገር አድርጓታል

የፀጥታና ደህንነት ተቋማት በመጠናከራቸው ኢትዮጵያን የማትበገርና የጸናች ሀገር አድርጓታል

ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷን፣ ሰላሟንና የሕዝቦቿን ደህንነት ለማስጠበቅ ባለፉት ዓመታት በጸጥታና ደህንነት ዘርፍ በተቋማዊ አደረጃጀት፣ በሕግ፣ በሙያዊ አቅም ግንባታ፣ በዘመናዊ ቴክኖሎጂና በተቀናጀ አሠራር ያካሄደቻቸው ሪፎርሞች የጸጥታ አቅሟን እንድታሳድግ አስችለዋል።

በዚህም የፖሊስና የመረጃ ተቋማት የሚመሩበት የሕግ ማዕቀፍና ተቋማዊ አደረጃጀቶችን ከማጠናከር ባሻገር፣ ተቋማቱ የዘመኑን የጸጥታ ተግዳሮቶች መመከት የሚያስችላቸውን አቅም እንዲገነቡ ተደርጓል።

በመከላከያ ዘርፍም የሠራዊቱን አደረጃጀትና የማድረግ አቅም ማጎልበት፣ የቴክኖሎጂ አቅሙን ማጠናከር የሪፎርሙ የትኩረት አቅጣጫዎች ነበሩ። 

በዚህም የምድር ጦርን ጨምሮ የአየር ኃይልና የባሕር ኃይል አቅምን ማጠናከር እንዲሁም ከዘመናዊ የሰራዊት አሠራር ጋር የሚሄድ የወታደራዊ አቅም መገንባት በዚሁ አቅጣጫ ተካትቷል።


 

በቅርቡ በሃዋሳ በተካሄደ የኮማንዶ ምረቃ ሥነ-ሥርዓት ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንዳሉት፣ ኢትዮጵያ የሀገሪቱን ደህንነት ከማስጠበቅ ባለፈ በቀጣናውና በአፍሪካ ሰላምና ብልጽግና ላይ አስተዋፅዖ ማድረግ የሚችል በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ ኤሊት የጦር ኃይል ለመገንባት እየሠራች ነው።

በምድርና በአየር የነበረውን ወታደራዊ ሥልጠና ወደ ባሕር ማስፋፋትን ጨምሮ፣ የጦር ኃይሉን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ማጠናከርና የተለያዩ የውጊያ አቅሞችን ማሳደግ የሠራዊቱን ዘመናዊነት ለማረጋገጥ ከተወሰዱ አቅጣጫዎች መካከል መሆናቸውን መጠቆማቸው ይታወሳል።

በተመሳሳይ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፣ በ45ኛው የፅናት ኮርስ የኮማንዶ ምረቃ መርሃ ግብር ላይ እንዳሉት፣ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ሉዓላዊነትና ብሔራዊ ጥቅምን ለማስከበር የተጠናከረ ወታደራዊ አቅም እንዲኖረው ተሰርቷል።

የቴክኖሎጂ ግኝቶችን የታጠቅንበት ዘመን ላይ ነን ያሉት ፊልድ ማርሻሉ፣ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ውስጥና የውጭ ጠላቶች እንደማይችሏት ገልጸዋል።

የጸጥታ ተቋማት በተናጠል ከመሥራት ይልቅ በቅንጅት እንዲሠሩ ማድረግም በሪፎርሙ የተሰጠው ትኩረት ሌላው አቅጣጫ ነው። 


 

የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል፣ የኢትዮጵያ ፖሊስ ኮሚሽነሮችና የሰላምና ፀጥታ ኃላፊዎች ሀገራዊ የጋራ የፀጥታ መድረክ ላይ እንደገለጹት፣ የፌዴራል፣ የክልልና የከተማ የጸጥታ ተቋማት በጋራ በማቀድ፣ በመቀናጀትና ልምድ በመለዋወጥ የጋራ የጸጥታ ተልዕኮዎችን የሚያከናውኑበት አሠራር ተጠናክሯል።

ይህ የተቀናጀ አሠራር በተለያዩ ብሔራዊ ዝግጅቶችና የሀገራዊ ጸጥታ ተልዕኮዎች ወቅት የተቋማትን የጋራ አቅም ለመጠቀም መሠረት መሆኑ በቀደመ ማብራሪያዎች ጠቁመዋል።

የሳይበር ደህንነት የሀገራዊ ደህንነት አካል እየሆነ መምጣቱ የሪፎርሙ አንድ አካል እንዲሆን ተደርጓል።

በዚህ ረገድ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ትዕግስት ሃሚድ አምስተኛው ዙር ብሔራዊ የሳይበር ታለንት የሰመር ካምፕ ማስጀመሪያ መርሃግብር ላይ እንደገለጹት፤ አስተዳደሩ ተቋማዊ አቅሙን በማሳደግ ወሳኝ የመረጃ መሠረተ ልማቶችን ከሳይበር ጥቃቶች ለመጠበቅ የሰው ኃይል ልማት፣ የዝግጁነት አቅምና የተቋማት ትብብርን ማጠናከር ላይ በትኩረት እየሰራ ይገኛል።


 

የሳይበር ደህንነት የሀገሪቱን ዲጂታል ሽግግር ለማረጋገጥ ወሳኝ በመሆኑ በዘርፉ ብቁ የሰው ኃይል ማፍራትና የተቋማትን ዝግጁነት ማጠናከር ቀዳሚ ትኩረት ነው ብለዋል።

በአጠቃላይ በሀገሪቱ የጸጥታና ደህንነት ዘርፉ የተከናወኑት ሪፎርሞች የጸጥታና ደህንነት ሥርዓቱን በተቋማዊ አደረጃጀት፣ በሙያዊ ብቃት፣ በቴክኖሎጂና በቅንጅታዊ አሠራር ለማጠናከር ያለመ ሲሆን፣ ይህም ሀገሪቱ የራሷን የጸጥታ አቅም በማሳደግ ሉዓላዊነቷን፣ ሰላሟንና ብሔራዊ ጥቅሟን በበለጠ አቅም ለማስጠበቅ ያላትን ብቃት አጠናክሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም