ቀጥታ፡

ግብፅ የምታስተጋባው ተከታታይ ጩኸት ኢትዮጵያ ወንዞቿን በማልማት ከመጠቀም የሚያግዳት አይደለም 

አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 3/2018 (ኢዜአ)፡-ግብፅ የምታስተጋባው ተከታታይ ጩኸት ኢትዮጵያ ወንዞቿን በማልማት የኤሌክትሪክ ኃይል በማመንጨትና በመስኖ ልማት ከመጠቀም እንደማያግዳት የቀድሞው የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር አምባሳደር አለማየሁ ተገኑ ገለጹ።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የአፍሪካ ሕብረትን አጀንዳ 2063 ርዕይ የሚያሳካ፣ የራስ መተማመን መንፈስን ያጎናጸፈ የአፍሪካ ድል መሆኑንም ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት ግብፅ የምታስተጋባው ተከታታይ ጩኸት ኢትዮጵያ ወንዞቿን በማልማት የኤሌክትሪክ ኃይል ከማመንጨትና መስኖ ከመጠቀም የሚያግዳት እንዳልሆነም አስገንዝበዋል።

አምባሳደር አለማየሁ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ ታላቁን ሕዳሴ ግድብ ከመገንባቷ በፊት ለሺዎች ዘመናት የዓባይ ወንዝን ሳትጠቀም ቆይታለች።


 

ኢትዮጵያ የዓባይ ወንዝን አስመልክቶ የምታራምደውን የፍትሐዊና ምክንያታዊ ተጠቃሚነት መርህ በተለያዩ መድረኮች ከመግለጽም ባሻገር በጋራ የመጠቀም ጽኑ ፍላጎቷን ስታስረዳ መቆየቷን ገልጸዋል።

የግብፅን ኢ-ምክንያታዊ የውሃ አጠቃቀም ክርክር ያስታወሱት አምባሳደር አለማየሁ፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ቆሞ እንመካከር እስከማለት የደረሰ እንደነበርም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ታላቁን የሕዳሴ ግድብ ግንባታ እስከመጨረሻው ድረስ በማስቀጠል ምክንያታዊና ፍትሐዊ የውሃ ሀብት ተጠቃሚነት መርህ እንዲሰፍን ብርቱ ተጋድሎ ማድረጓን ጠቅሰዋል።

ለዚህም በሀገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ግድቡን በራስ አቅም ለመገንባት ያደረጉት ከፍተኛ ድጋፍና ተጋድሎ በጀግንነት የታጀበና አስደናቂ መሆኑን አስታውሰዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የአፍሪካ ሕብረትን አጀንዳ 2063 ርዕይ የሚያሳካ፣ የራስ መተማመን መንፈስን ያጎናጸፈ የአፍሪካ ድል መሆኑንም ገልጸዋል።

የአፍሪካ ሀገራትም ሕዝብና የውስጥ አቅማቸውን በመጠቀም እንደ ታላቁ ሕዳሴ ግድብ ያሉ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን መገንባት እንደሚችሉ ትምህርት የሰጠ የፓን አፍሪካኒዝም ፕሮጀክት መሆኑን አብራርተዋል።

የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ጳጉሜን 4 ቀን 2017 ዓ.ም. ሲመረቅ የጎረቤት ሀገራት የኢትዮጵያ ደስታ ተካፋይ የሆኑበትና የጋራ ተጠቃሚነትን ያበሰረ ወሳኝ ፕሮጀክት መሆኑን አንስተዋል።

የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ከሀገር ውስጥ ባሻገር ለቀጣናው ሀገራት የፈጠረው የኃይል ትስስርም የዓባይ ወንዝን ኢ-ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ትርክት የሰበረ ድል መሆኑን አስረድተዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ፍጻሜም በግብፅና በታችኞቹ ተፋሰስ ሀገራት አስተማማኝ የውሃ ፍሰት በመፍጠር ምንም ዓይነት ጉዳት እንደማይደርስባቸው በተጨባጭ ያረጋገጠ መሆኑን አስረድተዋል።

የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታም ድንበር ተሻጋሪ ወንዞችን ፍትሐዊና ምክንያታዊ ተጠቃሚነት ትብብርና መርህ በማብሰር አዲስ ምዕራፍ የከፈተ ታሪካዊ ክስተት መሆኑን አብራርተዋል።


 

የታላቁ ሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያን በዓባይ ወንዝ ያለመጠቀም ኢ-ፍትሐዊ አካሄድን በማፍረስ የናይል ትብብር ማዕቀፍ ስምምነት ወደ ሥራ ማስገባት እንዳስቻለም አብራርተዋል።

ግብፅ የኢትዮጵያን ዕድገትና ብልጽግና አትፈልግም ያሉት አምባሳደር አለማየሁ፤ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ተጠናቆም ግብፅ የምታስተጋባው ጩኸት የሀገሪቷን የፖለቲካ ሁኔታ ለማርገብ እንደሚጠቀሙበት አመልክተዋል።

ለአብነትም በዓለም አቀፉ የፀጥታው ምክር ቤት ጭምር ታይቶ በማይታወቅ መልኩ በውሃ ጉዳይ ኢትዮጵያን መሞገቷን አስታውሰዋል።

ኢትዮጵያ በቀጣይ የምትገነባቸው ግድቦችም አስተማማኝ የውሃ ፍሰትን በመፍጠር የግብፅን የውሃ ብክነት እንደሚታደጉ አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ የውሃ ሀብቶቿን ለመጠቀም የማንም ይሁንታ ሳያስፈልጋት ተጨማሪ ግድቦችን በመገንባት በመርህ ላይ በተመሠረተ መልኩ ልማቷን የማፋጠን ሙሉ መብት እንዳላት አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር በየዓመቱ የምትተክላቸው ችግኞችም የስነ-ምኅዳር ደኅንነትን በመጠበቅ ለውሃ ሀብት ጥበቃ ጉልህ ጠቀሜታ እንዳለው ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ አርሶ አደሮች በቢሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞችን በመትከል ለዓባይ ተፋሰስ ጥበቃ ላበረከቱት ጉልህ አስተዋጽኦም ግብፅ ካሳ መክፈል እንደሚኖርባት አስረድተዋል።

ግብፅ ዓባይን ለሺዎች ዘመናት በብቸኝነት በመጠቀም ኢትዮጵያ ከልማት ወደኋላ እንድትቀር ላደረሰችባት በደልና ለአካባቢ ጥበቃ ለምታበረክተው አስተዋጽኦ ካሳ መክፈል እንዳለባትም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም