ቀጥታ፡

ትውልዱ በጀግኖች መስዋዕትነት የቆየችውን ሀገር ከነክብሯ የማጽናት አደራ አለበት 

ዲላ፤ ጳጉሜን 3/2018 (ኢዜአ)፡-ጀግኖች ለሀገራቸው ዋጋ ከፍለው ያቆዩዋትን ኢትዮጵያ የዛሬው ትውልድ ከነክብሯ የማጽናት አደራ አለበት ሲሉ የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዝናቡ ወልዴ (ዶ/ር) ገለጹ።

ጳጉሜን-3 የጽናት ቀን በጌዴኦ ዞን እና በዲላ ከተማ አስተዳደር በተለያዩ ዝግጅቶች በድምቀት ተከብሯል።


 

የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዝናቡ ወልዴ (ዶ/ር) በወቅቱ እንዳሉት ኢትዮጵያ በጀግኖች ልጆቿ መስዋዕትነት ለዘመናት ጸንታ የኖረችና በቅኝ ግዛት ያልተገዛች የጥቁር ህዝቦች ኩራት ናት።

በውስጥና በውጭ ጠላቶች በየዘመናቱ ኢትዮጵያን ለመበታተንና ለማፍረስ የተደረገው ጥረት በቁርጥ ቀን ልጆቿ ጽናትና የደም ዋጋ ጭምር ማክሸፍ ተችሏል ብለዋል። 

ይሁንና ዛሬም ባንዳና ባዳ ሀገራችን ኢትዮጵያን ለማዳከም ከታሪካዊ ጠላቶች ጋር ተባብረው እየሰሩ መሆኑን ያስታወሱት ዋና አስተዳዳሪው፣ በየዘመናቱ ጀግኖች ለሀገራቸው ዋጋ ከፍለው ያቆዩዋትን ኢትዮጵያ የዛሬው ትውልድም ከነክብሯ ማጽናት አደራ አለበት ብለዋል። 


 

በዚህም ትውልዱ በተለይ ወጣቱ የአካባቢውን ሰላም ከመጠበቅ ባለፈ ለሀገር ሁለንተናዊ እድገት የሚያደርገውን ጥረት ማጠናከር አለበት ሲሉ አሳስበዋል።

ጀግኖች አባቶች የደምና አጥንት ዋጋ ከፍለው ሉዓላዊነቷ የተከበረ ሀገር ለእኛ አስረክበውናል ያሉት ደግሞ የዲላ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ መስፍን ደምሴ (ዶ/ር) ናቸው።


 

ዛሬ የጽናት ቀን ሲከበር ከአባቶቻችን መስዋዕትነትና ጽናት በመማር ከድህነት የተላቀቀች ሀገር ለመገንባት በየዘርፉ በሚደረገው ጥረት በንቃት በመሳተፍና በማገዝ መሆን አለበት ብለዋል። 

ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በተሰማራበት መስክ ለሀገሩ በጽናት በመቆም ሕብረ ብሔራዊ አንድነቷና ሉዓላዊነቷ የተጠበቀ ኢትዮጵያን ለትውልድ ለማሻገር የበኩሉን እንዲወጣ አሳስበዋል።


 

በአከባበሩ ላይ የተገኙት የዲላ ከተማ ነዋሪው አቶ አለማየሁ ጅግሶ በበኩላቸው፤ የጽናት ቀን ሲከበር ለህዝቦች ሰላምና ለሀገር ሉዓላዊነት መስዋዕትነት የከፈሉ ባለውለታዎችን በማሰብ መሆኑ ተገቢ ነው ብለዋል።

ለከተማቸው ዘላቂ ሰላም ንቁ ተሳትፎ በማድረግ የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን ለማስቀጠል የበኩላቸውን እንደሚወጡም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም