የሀገርን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ በጽናት እየተጋን ነው - ኢዜአ አማርኛ
የሀገርን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ በጽናት እየተጋን ነው
ድሬዳዋ፤ ጳጉሜን 3/2018 (ኢዜአ)፡-የሀገርን ሉአላዊነት፤ ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ በጽናት እየተጉ መሆናቸውን የሀገር መከላከያ ሠራዊት እና የፀጥታ አባላት ገለጹ።
በድሬዳዋ የሚገኙ የሀገር መከላከያ ሠራዊት እና የፀጥታ አባላት የፅናት ቀንን በወታደራዊ ትርዒትና በሌሎች ስነ ስርአቶች አክብረዋል።
በቀኑ አከባበር ላይ የተሳተፉት የሀገር መከላከያ ሠራዊት እና የጸጥታ አባላት ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ የሀገርን ሉአላዊነትና ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ ከመቼውም ጊዜ በላይ በጽናት እየተጉ ነው። በዚህም ከህብረተሰቡ ጋር በቅንጅት እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
አስተያየታቸውን ከሰጡ የሀገር መከላከያ ሠራዊት አባላት መካከል መቶ አለቃ ማማሩ ታዬ እንዳስታወቁት፤ሠራዊቱ አንድነቱንና ህዝባዊነቱን ጠብቆ የሀገርን ሉአላዊነት ለማፅናት ተጋድሎውን አጠናክሯል።
ሠራዊቱ ከአባቶቹ የወረሰውን ጀግንነት በማስቀጠል የኢትዮጵያን ከፍታ ለማፅናት በቁርጠኝነት እየተጋ መሆኑን አስታውቀዋል።
የሀገር መከላከያ ሠራዊት የሀገርን ሉአላዊነት ከውጭና ከውስጥ ጠላቶች የመጠበቅ ተልዕኮውን በቁርጠኝነት እየተወጣ መሆኑን የገለጹት ደግሞ አስር አለቃ ምህረትዓለም ባደለ ናቸው።
የፅናት ቀን መከበሩ ሠራዊቱ ለሀገር መከበር ለከፈለው መስዋትነት እውቅናን በመስጠቱ ሰራዊቱ ግዳጁን በታላቅ ጀብድ ለመወጣት እንደሚያነሳሳው ጠቁመዋል።
የፅናት ቀን ሰላምና ፀጥታ በአስተማማኝ መንገድ የመጠበቅን ተልዕኮ በላቀ ደረጃ ለመወጣት ቃላቸውን ያደሱበት መሆኑን ያነሱት ደግሞ የፌደራል ፖሊስ አባል ዋና ሳጅን ጠብቀው መርድ ናቸው።
የድሬዳዋ አስተዳደር ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አባል ኮንስታብል ቅድስት ውብሸት በበኩላቸው፤ የፀጥታ መዋቅሮች ከህብረተሰቡ ጋር ትስስራቸውን በማጠናከር የነዋሪውን ሰላምና ፀጥታ በማረጋገጥ በላቀ ብቃት እየተወጡ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
በእለቱ ሀገርን በማፅናት እና ዘላቂ ሰላም በማረጋገጥ ተግባራት ላይ አበርክቶ ላላቸው ተቋማት የተዘጋጁ ሽልማቶች ተበርክተዋል።